ቀጥታ፡

በስፖርት ዘርፍ የተጀመረውን መነቃቃት ይበልጥ በማጎልበት ታዳጊ ወጣቶች ላይ እየተሰራ ነው

ጎሊና፣ ጥር 18/2018 (ኢዜአ)፡-በስፖርት ዘርፍ የተጀመረውን መነቃቃት ይበልጥ በማጎልበት ታዳጊ ወጣቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኘሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ተናገሩ።

ሰባተኛው መላው የአፋር ስፖርታዊ ውድድሮች በፈንቲ ረሱ ዞን ጎሊና ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

በመክፈቻ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንደገለጹት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች እየተካሄዱ ነው።

እንደ አገር እየተነቃቃ የመጣውን የስፖርት ዘርፍ በማጎልበት ታዳጊ ወጣቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በእግር ኳስ ዘርፍ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በክልሉ በስፖርት ዘርፍ የተጀመረውን ሥራ ለማጠናከር ፌዴሬሽኑ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ አቶ ሀሚድ ዱላ፣ የመላው አፋር ስፖርታዊ ውድድር አብሮነትና ወንድማማችነት የሚጎላበት ነው ብለዋል።

ስፖርታዊ ውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፣ በዚህ ውድድርም ከአፋር ባለፈ ሀገር የሚያስጠሩ ስፖርተኞች ሊወጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በክልሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ለማጠናከር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው እንዳሉት ስፖርታዊ ውድድሮች ጤናማና ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን በማፍራት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው።

በስፖርቱ ዘርፍ የተጀመረው መነቃቃት እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ዓመት በትራፊክ አደጋ ሕይወቱ ላለፈው የዳጉ ስፖርት መስራች ኑር ሁሴን ዓሊ ቤተሰቦች የግማሽ ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ፌዴሬሽኑ ለዚህ ዓመት የእግር ኳስ መወዳደሪያ የሚሆኑ 23 ኳሶችንም አበርክቷል።

በውድድሩ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ዮሐንሰ ሳህሌና የቀድሞ ተጫዋች አዳነ ግርማ፣ በአፋር ክልል በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎች እና የጎሊና ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም