የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ የሚያደርገውን ድጋፍ በዘላቂነት ለመቀጠል ቁርጠኛ ነው - የባንኩ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዌንቻይ ዣንግ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ የሚያደርገውን ድጋፍ በዘላቂነት ለመቀጠል ቁርጠኛ ነው - የባንኩ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዌንቻይ ዣንግ
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ በዘላቂነት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የባንኩ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዌንቻይ ዣንግ ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዌንቻይ ዣንግ ጋር ተወያይተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ ለማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራምን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የሪፎርም ፕሮግራሙ ኢኮኖሚውን በግሉ ዘርፍ እንዲመራ የማድረግ፣ የኢኮኖሚ እድገት ምንጮችን ማስፋት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚና ቱሪዝምን ማሳደግ እንዲሁም በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አማካኝነት ቀጣናዊ ትስስር የማጠናከር ግብ እንዳለው አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ቁልፍ ዘርፎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ እና የኢትዮጵያ ሪፎርምና የልማት የትኩረት መስኮች ላይ ያለውን ወሳኝ ሚና አድንቀዋል።
የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዌንቻይ ዣንግ የኢትዮጵያ መንግስት የእዳ እንደገና ማዋቀርን ጨምሮ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የወሰዳቸውን ጠንካራ እርምጃዎች ያደነቁ ሲሆን የተገኙ ለውጦችም አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ በተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች አማካኝነት የሚያደርገውን ዘላቂ የቴክኒክ እና ፋይናንስ ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው የኢትዮጵያ እና ዓለም ባንክ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የደረሰበትን ደረጃ ገምግመዋል።
በተለይም ከኢትዮጵያ የልማት ግቦች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ በባንኩ በኩል እየተደረጉ ያሉ የበጀት ድጋፎችና የፕሮጀክት ፋይናንስ አቅርቦት ላይ መምከራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።