ቀጥታ፡

 የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል - አቶ ገብረመስቀል ጫላ

ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተከናወኑ ሥራዎች በየዘርፉ ውጤት መመዝገቡን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።

የወላይታ ዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡን በማስመልከት "የጊፋታ ብስራቶች ለሕዝባችን ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ የተዘጋጀ ሲምፖዚየምና የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱ የተካሄደው የወላይታ ልማት የተቀናጀ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ በማተኮር ነው።


 

በመድረኩ ላይ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት፤ የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው፣ በቅርቡ መመዝገቡ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለህዝብ ባህል፣ ወግና የልማት ጥያቄዎች ትኩረት መሰጠቱን አስታውሰው፣ በዚህም በክልሉ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" ያሉትን እሴቶች በማጎልበትና የህዝብን አንድነት በማስቀጠል በየዘርፉ የልማት ግቦችን ለማሳካትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተዋል። 


 

ለዚህም በየአካባቢው ያሉትን ፀጋዎች ለይቶ በማልማት ለህዝብ ተጠቃሚነት ለማዋል መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

"ጊፋታ" ተገቢ እውቅና እንዲያገኝ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየሞች ሲዘጋጁ እና ምሁራንም በጉዳዩ ላይ ጥናት ሲያካሂዱ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።

"ጊፋታ" በዩኔስኮ እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።


 

የዞኑ አስተዳደር የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በየደረጃው ለመፍታት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዞኑን ገቢ ለማሳደግ በተደረገ ጥረት በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ስድስት ወር ብቻ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም ጠቅሰዋል። 

በዞኑ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 320 ባለሃብቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን፣ ለ42 ሺህ 397 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድልም እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዘርፎች ህዝቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በተለየ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለጹት።

በተለያዩ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የወላይታ ልማት የተቀናጀ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ መጀመሩንም አንስተዋል።


 

የወላይታ ሶዶ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መንግስቱ ትግሮ በበኩላቸው፤ ጊፋታ በዩኔስኮ መመዝገቡ በከተማው በፈጠረው መነቃቃት የቱሪስት ፍሰት እየጨመረ መጥቷል።

የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘምም የመዳረሻ ስፍራዎች ልማትና የጸጥታ ሥራ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ እየተመራ መሆኑን አመልክተዋል።

በመድረኩ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም