ቀጥታ፡

በመዲናዋ በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ለዜጎች ተጠቃሚነት በትኩረት ይሰራል

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት እንደሚሰራ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ''በትጋት አዲስ አበባን ወደ ላቀ ስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲያካሂድ የቆየው የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የመንግስትና የፓርቲ ሥራዎች አፈፃፀም ግምገማ ተጠናቅቋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማጠቃለያ መድረኩ ወቅት፤ መዲናዋን ውበትና ጸዳል ያላበሱ ዘመናዊ የመንገድ፣ የውሃ፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

አዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ የተከናወኑ የልማት ስኬቶችም የመዲናዋን የኮንፈረንስ ማዕከልነት በማሳደግ በርካታ ዜጎች በቱሪዝም ዘርፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል የተከናወኑ ተግባራትም የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የአገልግሎት እርካታ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የልማት አጋሮችና የህዝብን ተሳትፎ በማሳደግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በሰው ተኮር ልማት፣ በገበያ የምርት አቅርቦት ሥርዓት፣ በገበያ ማረጋጋትና ኑሮ ውድነት ቅንሳ፣ በዘላቂ ሰላም ግንባታና ተያያዥ የልማት መስኮችም አስደናቂ ስኬት ማምጣት እንደተቻለ አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፎች የተገኙ የልማት ስኬቶችም የአመራር ቁርጠኝነትና ተቀናጅቶ የመስራት ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።

በሚቀጥሉት በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራትም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በላቀ የመፈጸም አቅም የልማት ስኬቶችን ለማስቀጠል እንደሚሰራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አመራርም የመፈጸም አቅምን የበለጠ በማጎልበት በቤት ልማት፣ ቱሪዝም፣ መልካም አስተዳደር ስራዎችንና ገቢ አሰባሰብን በማጠናከር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም