ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃ የማይበገር የማህበረሰብ አቅም ለመገንባት ቁልፍ ሚና አለው - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃ የማይበገር የማህበረሰብ አቅም ለመገንባት ቁልፍ ሚና አለው - ኢጋድ
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃ የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባትና ለዘላቂ ልማት ጉልህ ሚና እንዳለው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አመለከተ።
ኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከል ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 72ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ምልከታ መድረክ(GHACOF 72) ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ ተጀምሯል።
“የአየር ንብረት መረጃ እና አገልግሎቶች መጠናከር፤ በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የአይበገሬ ማህበረሰቦችን ለመገንባትና ዘላቂ ልማት ያለው ሚና” የስብሰባው መሪ ሀሳብ ነው።
የኢጋድ አባል ሀገራት ባለስልጣናት፣ በቀጣናው የሚገኙ የአየር ንብረት ትንበያ ተቋማት፣ የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የአየር ንብረት መረጃ እና አገልግሎቶችን ማጠናከርና ማስፋት፣ ወቅታዊ መረጃዎችን ለውሳኔ መጠቀም፣ አይበገሬነትን መገንባትና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ የመድረኩ አበይት ትኩረቶች ናቸው።
በተለይም የአየር ትንበያዎች፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶች፣ ቴክኖሎጂዎች መጠቀምና ወቅትን ጠብቀው የሚወጡ መረጃዎች ድርቅና ጎርፍን ጨምሮ ሌሎች አደጋዎችን አስቀድሞ በመካለከልና የምላሽ አቅምን በማጠናከር ረገድ ያላቸውን ሚና አስመልክቶ ምክክር ይደረጋል።
የአየር ንብረት መረጃን የምግብ ዋስትና፣ የኢኮኖሚ መረጋጋትትና ዘላቂ አካባቢ ጥበቃን ጨምሮ ከሌሎች የልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ውጤት ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ይወያያሉ።
በስብሰባው የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከል ከእ.አ.አ ማርች እስከ ሜይ የዝናብ ወቅት ያለውን ቀጣናዊ የአየር ትንበያ መረጃ ይፋ ያደርጋል።
ትንበያው ለግብርና፣ ውሃ፣ ጤና እና ለአደጋ ዝግጁነት ያለው ፋይዳ ውይይት እንደሚደረግበት ኢዜአ ከማዕከሉ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶችን መቀነስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለፖሊሲ አውጪዎችና የልማት አጋሮች ምክረ ሀሳቦችንና ስትራቴጂካዊ ሰነዶችን ያቀርባሉ።
ኢጋድ በአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከሉ አማካኝነት የአየር ትንበያ መረጃዎችን በየጊዜው በማውጣትና የአባል ሀገራትን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ማጠናከር የሚያስችሉ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አመልክቷል።
የሞባይል ስልኮች እና ሌሎች የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች የግብርናና አየር ንብረት የማማከር አገልግሎቶች ኢኒሼቲቭ(DACAS ) እየተገበረ እንደሚገኝም ገልጿል።
ቀጣናዊ ተቋሙ ከእ.አ.አ 2023 አንስቶ ለሰባት ዓመታት የሚቆይ ቀጣናዊ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስትራቴጂን በመቅረጽ አባል ሀገራት እንዲተገብሩ አድርጓል።
ድንበር ተሻጋሪ የአይበገሬነት አቅምን የሚገነቡ ፕሮግራሞች፣ ጤና እና ምግብን ጨምሮ ዘርፍ ተኮር ትብብርን ማጠናከር፣ አቅም ግንባታ፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የእውቀት ሽግግር መድረኮችን ማዘጋጀት በአየር ንብረት አገልግሎት እና አይበገሬነት እያከናወናቸው ካሉ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የአፍሪካ ቀንድ ድርቅ እና ጎርፍን ጨምሮ ለሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭ ቀጣና ሲሆን ይህም በምግብ ዋስትና፣ የውሃ አቅርቦት፣ ጤና፣ መሰረተ ልማት እና ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድር ምክንያት ሆኗል።
ዛሬ የተጀመረው ቀጣናዊ ውይይት የአየር ንብረት ሳይንስን ለአስቀድሞ መከላከልና ምላሽ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ በማሳለጥ ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ድርጅቱ አመልክቷል።
በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት የዜጎችን ህይወትና የአኗኗር ሁኔታ ለመጠበቅ እንዲሁም ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች የማይገበር አቅም መገንባትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገልጿል።
72ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ምልከታ መድረክ (GHACOF 72) እስከ ነገ ይቆያል።