ቀጥታ፡

ባህል እየሆነ የመጣው የተፋሰስ ልማት የቡና ምርታማነትን እያሳደገ ነው 

ዲላ ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ በጌዴኦ ዞን ባህል እየሆነ የመጣው የተፋሰስ ልማት የቡና ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ገለጹ።

በዞኑ የ2018 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በገደብ ወረዳ ሐርሙፎ ቀበሌ አዳሜ ሃገሌ ተፋሰስ ተጀምሯል።


 

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የተፋሰስ ልማት የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ተጠብቆ እንዲቆይ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በዞኑ ባህል መሆኑን ተከትሎ በተለይም ከፍተኛ ተዳፋት በሆኑ የዞኑ መልክዓ ምድር የቡና ምርታማነትን በአማካይ በሄክታር ከ10 ኩንታል ማላቅ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የውሃ መጠንን በማሳደግ በምርትና ምርታማነት የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል በተያዘው ዓመትም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተው አርሶ አደሩ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

‎‎በዞኑ በ132 ንዑስ ተፋሰሶች 67 ሺህ 402 ሄክታር መሬት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እንደሚሸፈን ያነሱት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ ናቸው።


 

በዚህም ከ386 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

‎‎ለአንድ ወር በሚቆየው በዚሁ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን ከቡና፣ ከእንሰትና ፍራፍሬ ልማት ጋር በማቀናጀት እንደሚተገበር ተናግረዋል።

በዘመቻው ተሳታፊ የሆኑ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የተፋሰስ ልማት ስራ የመሬት እርጥበትን በመጨመር የግብርና ምርታማነትን በማሳደጉ የእርሻ ሥራቸው አካል አድርገው እየተገበሩት ነው፡፡


 

አርሶ አደር ታምራት ታደሰ ፤ ባለፉት ዓመታት በተፋሰስ ልማት ያከናወኑት የእርከንና የአፈር ካባ ሥራ የመሬት መከላትን በማስቀረት እርጥበት መጨመሩን አንስተዋል።

ይህም የእርሻ መሬታቸውን ለምነት በማሳደግ የቡናና እንሰት ምርታማነትን ማሳደጉን አንስተው በአሁኑ ወቅትም የእርሻ ሥራቸው አካል በማድረግ እየተገበሩት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለይም ውሃን ማቆየት የሚችሉትን እርከንና የጉድጓድ ቁፋሮ በዘመቻ እየተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፋሰስ ልማት የተራቆቱና ለአደጋ የተጋለጡ አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱ እገዛ ማድረጉን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

ቀበሌያቸው ተዳፋት መሆኑን ተከትሎ ለም የእርሻ መሬታቸውን በጎርፍ ከመወሰድ በመከላከል ለግብርና ልማት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የዞንና የሁሉም መዋቅሮች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አርሶ አደሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም