ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለትውልዱ ሰላምና ልማቷ የተረጋገጠ ጠንካራ ሀገር ለማስረከብ ዕድል ይፈጥራል

ድሬደዋ ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለትውልዱ ሰላምና ልማቷ የተረጋገጠ ጠንካራ ሀገር ለማስረከብ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን በድሬዳዋ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ የቆዩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

እስካሁን ባለው ሂደትም ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ ሁሉም አካባቢዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች የተካተቱበት የአጀንዳ ማሰባሰብና ልየታ ሥራዎችን አከናውኗል።

በሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ ታጣቂዎችን ጨምሮ በሀገር ወስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው መጻዒ ዕጣ ፈንታ ላይ ተመካክረውና ተወያይተው የተሻለ ሀሳብ ማዋጣት የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል።

በቅርቡ በትግራይ ክልል ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ሲጠናቀቅም ወደ ዋና አጀንዳ ውይይት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በድሬዳዋ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞት የመጣው የገዘፈ ዓላማ እውን እንዲሆን ኃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።


 

የኃይማኖት አባት ቦጋለ ሰዒዳ እንደተናገሩት፣ ሀገራዊ ምክክሩ የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከልና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን ለማዳበር ጉልህ ፋይዳ አለው።

ሰላምና ልማቷ የተረጋገጠ ጠንካራ አገር ለትውልዱ ለማስተላለፍም  መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኃይማኖት ተቋማት በሰላም እሴትና በወል ትርክት ግንባታ ላይ የድርሻቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛሉም ብለዋል።

የኃይማኖት ተቋማትና ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተመሳሳይ ተልዕኮ ያነገቡ በመሆኑ ለሰላም፣ ለልማትና ብሄራዊ መግባባት መፈጠር በቁርጠኝነት ይሰራሉ ብለዋል።


 

የአፍረን ቀሎ አባገዳ አብዱራዛቅ አህመድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ  የአጀንዳዎች ልየታ ሥራ ማከናወኑንና በዚህም አባገዳዎች በንቃት መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታት የሀገርን ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት ለማፅናት ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የግጭት አፈታት ዘዴዎች የተዛቡ ትርክቶችንና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት አጋዥ ሚና እንደሚጫወቱ የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ የሀገር ሽማግሌ ዩሱፍ ሐሰን ናቸው።


 

ሀገራዊ ምክክሩ ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታና ለወል ትርክት ግንባታ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው፣ የሀገር ሽማግሌዎች ከኮሚሽኑ ጎን በመቆም ያላቸውን ልምድ ለማካፈልና በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም