ኢትዮጵያ ለጀመረችው አረንጓዴ የኢኮኖሚ ሽግግር አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለጀመረችው አረንጓዴ የኢኮኖሚ ሽግግር አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለጀመረችው አረንጓዴ የኢኮኖሚ ሽግግር አስተማማኝና ተመጣጣኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) ገለፁ።
የቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ እና የኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ዓላማን የሰነቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መስርተዋል።
የአጋርነት ስምምነቱን የኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እድሪስ አደም እና የቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ከፍተኛ ተወካይ ዣኦ ዚዪ ተፈራርመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዘመናዊ መልክ ለጀመረችው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው።
ኃይል የኢንዱስትሪ ልማት ሞተር ብቻ ሳይሆን፣ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ ያለ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፈጠራን ማስፋፋትም ሆነ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻልም ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በብሔራዊ የኃይል መስመር ላይ ብቻ ጥገኛ ሳትሆን ሚኒ-ግሪድ እና ሃይብሪድ የታዳሽ ኃይል ሥርዓቶችን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህም በገጠር የሚገኙ ስራ ፈጣሪዎችና ማህበረሰቦችም እኩል የዲጂታል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ እና በቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ መካከል የተመሰረተው አጋርነት ዘመናዊ የኃይል ማከፋፈያና ማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ያስችላል ብለዋል።
የኃይል መፍትሔ መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ የመገጣጠም እና የማምረት አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ስልጠና ለመስጠት እድል እንደሚፈጥርም ነው የገለፁት።
የሀገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት ለሚሰሩ ኩባንያዎች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።
የኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እድሪስ አደም በበኩላቸው፣ ኤዳን ፓወር በኢትዮጵያ የሀይል እድገት ውስጥ ለ20 ዓመታት አጋር ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሟላት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት በጋራ ለመስራት ትልቅ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
የቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ከፍተኛ ተወካይ ዣኦ ዚዪ እንዳሉት፣ይህ አጋርነት የቻይናን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚያስችል ነው።