የማርበርግ ቫይረስ በዜጎች ላይ ሊያደርስ የነበረውን አስከፊ ጉዳት በጠንካራ የበሽታ መከላከል ሥርዓት መቆጣጠር ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የማርበርግ ቫይረስ በዜጎች ላይ ሊያደርስ የነበረውን አስከፊ ጉዳት በጠንካራ የበሽታ መከላከል ሥርዓት መቆጣጠር ተችሏል
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ ማርበርግ ቫይረስ ሊያደርስ የነበረውን አስከፊ ጉዳት በተቀናጀና ጠንካራ የበሽታ መከላከል ሥርዓት መቆጣጠር መቻሉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል በወሰደችው የተቀናጀና አስቸኳይ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት ቫይረሱን ጨርሶ ማጥፋት ችላለች።
በዚህም ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በመከላከል በወርሃ ጥቅምት ተከስቶ የነበረውን የማርበርግን ቫይረስ ከወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሏን ተከትሎ የዕውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የበሽታ መከላከል የካበተ ልምድና ተሞክሮዋን በመጠቀም የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ መስጠት ችላለች ብለዋል።
በዚህም በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ የማርበርግ ቫይረስ ሊያደርስ የነበረውን አስከፊ ጉዳት በተቀናጀና ጠንካራ የበሽታ መከላከል ሥርዓት የበሽታ ሥርጭቱን ማምከን እንደተቻለ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ ሥርጭትን የተቆጣጠረችበት ሥርዓትም ሳይንሳዊ መመሪያና ነባራዊ ሁኔታን አጣጥሞ የመተግበር ውጤት ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የማርበርግ በሽታ ሥርጭት ፈጣን የመቆጣጠር ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት ለአፍሪካ ምሳሌ ይሆናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ውጤቱም ህብረተሰቡ መንግስት የሚሰጠውን መመሪያ ገቢራዊ በማድረጉ የመጣ ነው ብለዋል።
የፌደራልና የክልል ጤና ተቋማት እንዲሁም የጤና ሙያተኞች የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ላበረከቱት በትብብር ላይ የተመሰረተ አስደናቂ ቅንጅት ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን የማይበገርና ፈጣን የጤና ምላሽ አሰጣጥ አቅም የበለጠ በማጎልበት የዜጎችን የጤና አገልግሎት ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።