ያገኘነውን የተሀድሶ ስልጠና በመተግበር ለሰላምና ልማት የበኩላችንን እንወጣለን-የቀድሞ ታጣቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
ያገኘነውን የተሀድሶ ስልጠና በመተግበር ለሰላምና ልማት የበኩላችንን እንወጣለን-የቀድሞ ታጣቂዎች
ደብረ ብርሃን/ደሴ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦የወሰዱትን የተሀድሶ ስልጠና ተግባር ላይ በማዋል ለዘላቂ ሰላምና ልማት መጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ በደብረ ብርሃንና በኮምቦልቻ ጊዜያዊ የተሃድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል ሥልጠና የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።
በደብረ ብርሃን ከተማ ጊዜያዊ የተሃድሶ ስልጠና ማዕከል ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል ወጣት ሙሉቀን መስፍን ለኢዜአ እንዳለው፤ በጫካ የሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድን የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ ጠላቶች መጠቀሚያ ጭምር መሆኑን በመረዳት የመንግስትን የሰላም አማራጭ ተቀብሎ መምጣቱንና ባገኘው የተሀድሶ ስልጠና መሰረትም ወደ መደበኛ የልማት ሥራው ለመመለስ እየተዘጋጀ ነው።
የሃምሳ አለቃ ፈለቀ ሰጤ በበኩላቸው፤ በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ ገብተው ህዝቡን ለተለያዩ ችግሮችና ለስቃይ ሲዳርጉ በመቆየታቸው መጸጸታቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ከጥፋት ድርጊታቸው ተምረው የሰላም አማራጭን በመቀበል በተሃድሶ ስልጠና የበደሉትን ህዝብ በልማት ለመካስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
ሌሎች የጥፋት ቡድኑ አባላትም መንግስት ያቀረበውን የሰላም መንገድ ተቀብለው እንዲመጡ ከራሳቸው ልምድ በመነሳት መክረዋል።
በኮምቦልቻ ጊዜያዊ የተሃድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠና ከወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል ደረበ ጌታዬ፤ ጥያቄዎችን በሰላም የመፍታት አማራጭን ትተው ጫካ በመግባት ህዝብ የሚገለገልባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት በማውደማቸው መጸጸታቸውን ገልጸዋል።
ከስህተታቸው በመማር ወደሰላም መምጣታቸውን ተናግረው፣ በተሀድሶ ስልጠና ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የሰላም አምባሳደር ሆነው ለመስራት መነሳታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የቀድሞ ታጣቂ ባለሟል ምስጋናው በበኩላቸው፤ በጫካ ሲንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት ለሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና ስቃይ ምክንያት በመሆኑ ተቆጭተው የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ የበደሉትን ህዝብ በልማትና በሰላም ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውንና በተሀድሶ ስልጠናም መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
የሰላም አማራጭን በመከተል ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በሚደረግ ጥረት ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻዬን እወጣለሁ ያለችው ደግሞ ፀሐይ ታደሰ ናት።