ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ የሆነችበት መንገድ የጠንካራ የአመራር ብቃት ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ የሆነችበት መንገድ የጠንካራ የአመራር ብቃት ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ የሆነችበት መንገድ የጠንካራ የአመራር ብቃት ማሳያ መሆኑ የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጂን ካሴያ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል በወሰደችው የተቀናጀ እና አስቸኳይ ምላሽ ቫይረሱን ማጥፋት ችላለች።
በዚህም ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሏን ተከትሎ የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የክልል ርዕሳነ መስተደድሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጂን ካሴያ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ጠንካራ ርምጃ ወስዳለች።
ይህም ንቁ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ያስመዘገበችው ውጤት መሆኑን በማንሳት፣ ጠንካራ የመከላከል አቅሟን ይገልጻል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ የሆነችበት መንገድ የጠንካራ የአመራር ብቃት ማሳያ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ማዕከሉ በሽታውን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ግብዓቶችን በማቅረብ ከኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከላከል ግብረ ሀይል ጋር በትብብር መስራቱን ጨምረው አስታውቀዋል።
ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ፤ ለኢትዮጵያ የበሽታ መከላከል ስርዓት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ ነፃ የሆነችበት መንገድ የመንግስትና የማህበረሰቡን ትብብር እንደሚያሳይ አንስተዋል።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በዓለም ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት ኢትዮጵያ በግልፅና የተቀናጀ የበሽታ መከላከል ስርዓት ቫይረሱን መቆጣጠር ችላለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ በመንግሥት፣ በጤና ተቋማት እና በማህበረሰቡ መካከል የነበረው ትብብር በተግባር ለውጥ ማምጣቱን አይተንበታል ነው ያሉት።