ቀጥታ፡

ሰብላችንን በወቅቱ ሰብስበን በማጠናቀቅ ወደ ቀጣይ ተግባራት ተሸጋግረናል - አርሶአደሮች

ደብረ ማርቆስ፤ ጥር 18 /2018 (ኢዜአ)፡- በመኸር ያለሙትን ሰብል በወቅቱ ሰብስበው በማጠናቀቅ ወደ ሌሎች የመስኖ እና እንስሣት ዕርባታ ተግባራት መሸጋገራቸውን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶአደሮች ተናገሩ።

በዞኑ የአዋበል ወረዳ ወጀል ቀበሌ እንዲሁም የአነደድ ወረዳ እነችፎ ቀበሌ አርሶአደሮች ምሥጋናው የኔው እና አጉማሱ አታላይ እንዳሉት፤ በመኸር እርሻ ያለሙትን ሰብል በወቅቱ መሰብሰባቸው በዝናብ እንዳይበላሽና የምርት ብክነት እንዳከሰት አስችሏል።


 

የደረሱ ሰብሎችን በደቦ በወቅቱ መሰብሰብ አርሶአደሩ ጊዜን በአግባቡ እንዲጠቀምና ምርትና ምርታማነቱ እንዲጨምር የጎላ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል።

የመኸር ሥራን በማጠናቀቃቸው ወደ መስኖና እንስሣት ዕርባታ ሥራ መሸጋገራቸውንም ለኢዜአ አረጋግጠዋል።


 

በዞኑ በመኸር ከተሸፈነው ከ640 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ ከ625 ሺህ ሔክታር የሚልቀው ሰብል መሰብሰቡን በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ እምቢአለ አለኸኝ አስታውቀዋል።

 


ቀሪው በሁለት ሳምንታት ውስጥ ተሰብስቦ እንደሚጠናቀቅም አመላክተዋል።

የምርት ብክነት እንዳይኖር በሜካናይዜሽና በሰው ኃይል በጥንቃቄ ምርት መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

በምርት ዘመኑ ከለማው ሰብል ከ25 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም