ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመቆጣጠር ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆናለች - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመቆጣጠር ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆናለች - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በተቀናጀ እና ጠንካራ የበሽታ መከላከል ስልት የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመቆጣጠር ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆኗን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል በወሰደችው የተቀናጀና አስቸኳይ ምላሽ ቫይረሱን ከኢትዮጵያ ማጥፋት እንደተቻለ ተገልጿል።
በዚህም ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በመከላከል በወርሀ ጥቅምት ተከስቶ የነበረውን የማርበርግን ቫይረስ ከወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሏን ተከትሎ የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በተቀናጀ የጤና ስርዓት ውጤታማ የበሽታ መከላከል ስራዎችን አከናወናለች።
ኢትዮጵያ በተቀናጀና ጠንካራ የበሽታ መከላከያ ስልትን በመተግበር የወባ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽን እና ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በብቃት በመከላከል ጠንካራ አቅም እንዳላት አሳይታለች ብለዋል።
በወርሀ ጥቅምት በጅንካ ከተማ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ በተቀናጀ የጤና ስርዓትና አገልግሎት ነፃ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ ነፃ የሆነችው በጋራ ጥረትና ርብርብ መሆኑን በማንሳት፣ ስንተባበር የማናሸንፈው ችግር እንደሌለ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተቀናጀና በተደራጀ የበሽታ መከላከያ ስርዓት ከቫይረሱ ነፃ በመሆኗ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።