የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ከመቻል ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ከመቻል ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀም ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይስተናገዱበታል።
ኢትዮጵያ መድን ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን 16 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ16ቱ ጨዋታዎች 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
መድን በ18 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው መቻል እስከ አሁን ባከናወናቸው 16 ጨዋታዎች በሰባቱ አሸንፎ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዶ አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 22 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
መቻል በ26 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮጵያ መድን ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ይጫወታል። መቻል ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምድረ ገነት ሽሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታዎች ያደርጋሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች በስድስቱ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 15 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 12 ጎሎች አስተናግዷል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ22 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ምድረ ገነት ሽሬ በበኩሉ 16 ጨዋታዎችን አድርጎ ያሸነፈው በአምስቱ ነው። ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ በአምስቱ አቻ ተለያይቷል። በ16ቱ ጨዋታዎች ላይ 16 ጎሎችን ሲያገባ በተመሳሳይ 13 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ምድረ ገነት ሽሬ በ20 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16ኛ ሳምንት በመቻል ካስተናገደው ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ይጫወታል። ምድረ ገነት ሽሬ ካሸነፈ ተከታታይ ድል ያስመዘግባል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወላይታ ድቻ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ወላይታ ድቻ በ14 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በ16ኛው ሳምንት በመቀሌ 70 እንደርታ ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት ስድስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ድል የናፈቀው ወላይታ ድቻ ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እድል ሊሰጠው ይችላል።