በተጠባቂው ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉ መሪ አርሰናልን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉ መሪ አርሰናልን አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ አርሰናልን 3 ለ 2 አሸንፏል።
ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ብሪያን ምቡዌሞ፣ ፓትሪክ ዶርጉ እና ማትያስ ኩንሃ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
ሚኬል ሜሪኖ እና የማንችስተር ዩናይትዱ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በራሱ ላይ ለአርሰናል ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ማትያስ ኩንሃ በ87ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት አስደናቂ ግብ ዩናይትድን አሸናፊ አድርጓል።
በጨዋታው አርሰናል የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና ጥሩ የግብ እድሎችን ቢፈጥርም ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር አልቻለም።
ማንችስተር ዩናይትድ በመልሶ ማጥቃት ያደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ አድርጎታል።
በሊጉ 10ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ዩናይትድ በ38 ነጥብ ደረጃውን ከአምስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል።
ዩናይትድ አርሰናልን ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ አሸንፏል።
በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው የሊጉ መሪ አርሰናል 50 ነጥብ ላይ ረግቷል።
መድፈኞቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሜዳው በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ባለፉት ሶስት የሊጉ ተከታታይ ማሸነፍ አልቻሉም።
አርሰናል ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ብሏል።
ዛሬ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ቼልሲ ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 1 ሲያሸንፍ አስቶንቪላ ኒውካስትል ዩናይትድን እና ኖቲንግሃም ፎረስት ብሬንትፎርድን በተመሳሳይ 2 ለ 0 አሸንፈዋል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ23 ሳምንት መርሐ-ግብር ነገ ኤቨርተን እና ሊድስ ዩናይትድ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል።