በመዲናዋ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው
አዲስ አበባ ፤ጥር 17/2018 (ኢዜአ)፡-በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት በመዲናዋ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ተቋማት ገለጹ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃጸምና የቀጣይ የትኩረት መስኮች የግምገማ ምክክር መድረክ ሁለተኛ ቀን ውሎ መካሄዱን ቀጥሏል።
በሁለተኛው ቀን ውሎው የግምገማ የምክክር መድረክ ተሳታፊ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የመዲናዋን ዕድገት የሚያስቀጥሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ፤በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
የመዲናዋን ነዋሪዎች የቤት አቅርቦት ፍላጎት ለማጣጣም በመንግስት የግል አጋርነት፣ በማኅበር ፤በሪል ስቴትና በግል የቤት ልማት አማራጭ በማስፋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለያዩ አማራጮች በመዲናዋ የተገነቡና በግንባታ ሂደት የሚገኙ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን የቤት አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ፤ በበጀት ዓመቱ የመዲናዋን የትራንስፖርት ሥርዓት የሚያሳልጥ የመንገድ መሰረተ ልማት መገንባቱን ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራትም በግንባታ ሂደት የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዘሪሁን አባተ እንደገለጹት፤ የመዲናዋን የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም አዳዲስ የውሃ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግና ነባር የውሃ ፕሮጀክቶችን ደረጃና ጥራት በማሻሻል የውሃ አቅርቦት አቅምን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ