ቀጥታ፡

የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ የህብረተሰቡን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ እና የወላይታ ልማት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ገብረመስቀል ጫላ አስታወቁ።

የልማት ማህበሩ 25ኛ ዓመት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።


 

አቶ ገብረመስቀል ጫላ በጉባኤው እንደገለጹት ጠንካራ የስራ ባህል በማስረጽ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ማህበሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ ይገኛል።

ማህበሩ በተለይም የህብረተሰቡን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የህብረተሰቡን አንድነት በበለጠ በማጠናከር ተግባሩን ማስቀጠል እንደሚገባው አመላክተዋል።


 

ግብርናን በማዘመን ህዝቡን ከጠባቂነት ለማውጣትና የተሻለ ኑሮ እንዲመራ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ማህበሩ የያዘው ራዕይ እንዲሳካ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው ለልማት ማህበሩ መጠናከር ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትን አመስግነዋል።

ልማት ማህበሩ መንግስት እያከናወነ ያለውን ስራ በማገዝ ለህዝቡ ልማት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።


 

በለውጡ መንግሥት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩ ምቹ ምህዳር መፈጠሩን አንስተው ቀጣይነት ያለው ውጤት እንዲያስመዘግብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ማህበሩን በዘላቂነት ለማጠናከር በህዝቡ ተሳትፎ እና በአጋር ተቋማት ትብብር ከ650 ሚሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።

የልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበባየሁ ቶራ(ዶ/ር) በበኩላቸው ማህበሩ ከአባላቱ፣ ከህዝቡና አጋር አካላት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የልማት ማህበሩ በትምህርት፣ በጤና፣ በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ እና በሰው ሀብት ልማት ዙሪያ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ለማህበሩ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም