ቀጥታ፡

በዞኑ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማስፈን የተከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል

ደብረ ማርቆስ ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማስፈን የተከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት ውጤት ማስገኘታቸውን የዞኑ አስተዳደር  አስታወቀ።

በዞኑ በግማሽ ዓመቱ የተከናወኑ የሰላም፤ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተገምግመዋል።


 

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ እንደገለጹት፤በዞኑ ዘላቂ ሰላምና ልማት  ለማረጋገጥ የተከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤናና ሌሎች መስኮች ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ በመሰራቱ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ሴክተሮች የተስተዋለውን የአፈጻጸም ውስንነት ለመፍታት የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ መቻሉን ተናግረዋል።

የዞኑ መስተዳደርም ለወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በቀጣይ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበበ መኮንን እንደገለጹት፤ በመኸር ሰብል ልማት ከ22 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ በቅድመ ምርት ግምገማ ተረጋግጧል። 


 

በበጋ መስኖ ልማቱም በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ በተደረገ ጥረት መቶ በመቶ ማሳካት መቻሉ የሚበረታታ ውጤት  መሆኑን አመልክተዋል።

የዞኑ ስራና ክህሎት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጸሃይ ቦጋለ በበኩላቸው፤ መምሪያው ባለፉት ስድስት ወራት ከ55 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል ብለዋል። 


 

የስራ እድል ተጠቃሚ ለሆኑ ዜጎችም ከ120 ሚሊየን ብር በላይ የተዘዋዋሪና የመደበኛ ብድር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስገንዝበዋል።

በዛሬው መድረክ በሚቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም በቀጣይ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የዞኑን እድገት በማፋጠን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩ የቢሮ ሃላፊዎቹ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም