ስፖርት ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ያለውን አቅም ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ያለውን አቅም ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ነው
ጅማ፣ ጥር 17/2018(ኢዜአ) :-ስፖርት ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ያለውን አቅም ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው 10ኛው የመንግስት የዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ውድድር ፌስቲቫል ዛሬ እንግዶችና ተሳታፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ በመክፈቻው ስነ ስርአት ላይ እንዳሉት የስፖርት ዘርፉን ከመዝናኛነት ባለፈ ለአብሮነትንና ለወንድማማችነት ያለውን አቅም ለማጎልበት እየተሰራ ነው ።
ለዚህም መንግስት የስፖርት ማዘውተርያ መሰረተ ልማቶችን እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገራችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄደው የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ውድድርም በዘርፉ የተማሪዎችን ተሰጥኦ ለመለየት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም በላይ የስፖርት ፌስቲቫሉ የባህል እሴቶችን ለመለዋወጥም አወንታዊ ሚና አለው ብለዋል።
የጅማ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባ ፊጣ (ዶ/ር) በመክፈቻ ስነስርአቱ ላይ እንዳሉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ውድድር ፌስቲቫል ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ተማሪዎች በ15 የስፖርት አይነቶች ውድድር ያካሂዳሉ።
ለ15 ቀናት በሚቆየው የስፖርት ፌስቲቫል አብሮነትን እና ወንድማማችንነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አባይ በላይሁን በበኩላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ውድድር በተሻለ ብቃት ተመልሷል ብለዋል።
የስፖርት ፊስቲቫሉ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉ የስፖርት አቅምን ለማውጣት እና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
እንዲህ አይነት የስፖርት ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተደማሪ አቅም እንደሚሆኑ አንስተዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው የስፖርት ውድድርም ከ5ሺህ በላይ ከመላው ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተወዳዳሪ ተማሪዎች እየተሳተፉ መሆኑም በመክፈቻው ተመላክቷል።