በተለወጠ የሥራ ባህል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በተለወጠ የሥራ ባህል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለወጠ የሥራ ባህል በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የአስተዳደሩ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
የማስተባበሪያ ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ይመር ከበደ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ባለፉት ስድስት ወራት 24/7 የስራ ባህልን በመከተል በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የቤት ግንባታና እድሳት፣ ማዕድ ማጋራት፣ ደም ልገሳ እና የትራፊክ እንቅስቃሴን የማስተባበር ስራዎች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።
ባለፉት ስድስት ወራት ከ4ሺህ 900 በላይ ቤቶችን በመገንባት ለሀገር ባለውለታዎች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች መተላለፋቸውን አብራርተዋል።
በከተማዋ አቅመ ደካማ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር መከናወኑን ነው የገለፁት።
በስድስት ወራት ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውንና በቀጣይም የህብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።