ቀጥታ፡

በክልሉ የህፃናት መቀንጨርና መቀጨጭን ለመቅረፍ ምግብና ስርዓተ ምግብ ላይ ይሰራል

አዳማ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል  የህፃናት መቀንጨርና መቀጨጭ ችግሮችን ለመቅረፍ  ለምግብና ስርዓተ ምግብ  ትኩረት መሰጠቱን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ  ሳዳት ነሻ ገለፁ።

የኦሮሚያ ክልል የምግብና ስነ ምግብ ምክር ቤት በክልሉ የህፃናት መቀንጨርና መቀጨጭን ችግሮችን ለመቅረፍ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ የምምክር   መድረክ  በአዳማ  አካሄዷል ።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ እንደገለፁት በክልሉ  የህፃናት መቀንጨርና መቀጨጭ ችግሮችን ለመቅረፍ  የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ።


 

በተለይም ችግሩን ለመቅረፍ  ለምግብና ስርዓተ ምግብ  ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የኦሮሚያ የምግብና ስነ ምግብ ምክር ቤትም እስከ ወረዳ ድረስ  አደረጃጀት በማዋቀር  በቀዳማይ ልጅነት ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ከጽንስ እስከ ስድስት ዓመት ዕድሜ ያሉ ሕጻናት በአዕምሮ እና በአካል እንዲበለጽጉ የማድረግ ዓላማን አንግቦ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በምግብና ስነ ምግብ እጥረት የሚከሰቱ  የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግሮችን ለመቀነስ በእናቶች፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በግብርና፣ በትምህርትና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

መድረኩም በክልሉ  የምግብና ስርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመቅረፍ የተሰሩ ስራዎችን በአግባቡ በመፈተሽ በቀጣይ የተቀናጀ ጥረት ለማድረግ መሆኑንም አስገንዝበዋል ።


 

በሰቆጣ ቃልኪዳን የሞዴል ወረዳዎች ኢንሼቲቪ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ እስራኤል ሃይሉ በመድረኩ ላይ  ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳመለከቱት  የሰቆጣ ቃልኪዳን በሁሉም ክልሎች ከ500 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች የህፃናት መቀንጨርና መቀጨጭ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የህፃናትን መቀንጨር ዜሮ ለማድረግ በተጀመሩ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ለዚህም በመደኛነት እየተከናወኑ ካሉት ስራዎች መካከል በምግብና ስርዓተ ምግብ  ውጤታማ ለማድረግ በወተት፣ በማር፣ በዶሮ፣ ዓሣ  ልማት ላይ መሰራቱን አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም