ቀጥታ፡

በክልሉ የጤና ተቋማትን አገልግሎት አስጣጥ ለማሳደግ ለህብረተሰብ ተሳትፎ ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ ፤ጥር 17/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የጤና ተቋማትን አገልግሎት አስጣጥ ለማሳደግ  ለህብረተሰብ ተሳትፎ  ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን  ቡድን በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰትና ሉሜ ወረዳዎች በመገኘት በጤና አገልግሎት  በተሰሩ ሞዴል ስራዎች ላይ  የልምድ ልውውጥ  አድርጓል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ አማካሪ አቶ አብዱረዛቅ አህመድ ለኢዜአ እንዳሳታወቁት በክልሉ  የጤና አገልግሎት  ጥራት፣ ፍትሃዊነትና ደህንነት ለማረጋገጥ  እየተሰራ ነው።

ለስኬቱም  የጤና ተቋማትን በግብአትና በሰው ሀይል ለማሟላትና ጽዱ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ   እንደሆነ ገልጸዋል።


 

የጤና ተቋማቱን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የመድሀኒት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶች በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ መገንባታቸውን አመልክተዋል።

የማህበረሰቡን የጤና ዋስትና ለማረጋገጥም በአነስተኛ ክፍያ ዓመቱን ሙሉ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የጤና መድህን አገልግሎት ማስፋፋት መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነትም ቤት ለቤት ትምህርት በመስጠት ህብረተሰቡ ከተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እራሱን እንዲከላከል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን አብሬ በበኩላቸው በዞኑ ጠንካራ የጤና አገልግሎትን ለመገንባት ከህበረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተሰራው ስራም የዞኑ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች  ሞዴል ሆነው እንዲወጡ መሰራቱን  ተናግረዋል።

በሆስፒታል ደረጃ ሲሰጡ የነበሩ አልትራሳውንድ የመሳሰሉ  ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን በ46 ጤና ጣቢያዎች በሟሟላት ህብረተሰቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

የጤና አገልግሎት መረጃን ዲጂታላይዝድ  ማድረግና ተቋማቱን  በማስዋብ  ለተገልጋይና ለባለሙያዎች ምቹ  ማድረግ ላይ መሰራቱን   ገልፀዋል ።

በምስራቅ ሸዋ ዞን የቦሰት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጉተማ ቢፍቱ የዲጂታል ጤና ቴክኖሎጂ ሥርዓትን ከማጠናከር እንዲሁም  ህክምና አገልግሎትን ከማዘምን ረገድ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ በህክምና ተቋማት የሚስተዋሉ የህክምና ግብዓቶችን ከሟሟላት ባለፈ ጤና ተቋማትን ለማስዋብ ከወረዳው በጀት መመደቡን ጠቅሰው ጤና ተቋማትም የውሰጥ ገቢያቸውን እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ፉአድ ጁአድ በሰጡት አስተያየት በቦሰት ወረዳ እና ወለንጪቲ ከተማ የሚገኙ ሞዴል ጤና ጣቢያና ጤና ኬላ አገልግሎት አሰጣጡ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል ።

በህክምና ተቋማቱ በተደረገው ሪፎርም የጤና ተቋማት በዘመናዊ መሳሪያዎችና በሰው ሃይል በሚገባ መደራጀታቸውን፣ ለተገልጋይና ለባለሙያዎች ምቹና ማራኪ  መደረጉን መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

በልምድ ልውውጡ ያገኙትን ተሞክሮ ወደ ዞኑ ጤና  ተቋማት ወስደው  በተግባር   ለማዋል እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም