በክልሉ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን በማቋቋም ህዝቡን በልማት እንዲክሱ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን በማቋቋም ህዝቡን በልማት እንዲክሱ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ጎንደር ፤ጥር 17/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን በአጭር ጊዜ በማቋቋም ህዝቡን በልማት እንዲክሱ የሚደረጉ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።
በብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን አስተባባሪነት በጠዳ የስልጠና ማእከል የተሀድሶ ስልጠና ሲከታተሉ ለቆዩ የቀድሞ ታጣቂዎች የሽኝትና የምረቃ ስነ ስርአት ዛሬ ተከናውኗል።
በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ በሪሁን መንግስቴ እንደተናገሩት የዘላቂ ሠላም ስምምነቱ ክልሉን ወደ ተሟላ ሠላም ለማሸጋገር ምቹ መደላድል ፈጥሯል።
በሠላም ስምምነቱ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የሠላም አማራጭን በመከተል መግባታቸውን ጠቁመው የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ የማቀላቀል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የቀድሞ ታጣቂዎች በመረጡት የስራ መስክ ተሰማርተው እራሳቸውን ማቋቋም እንዲችሉና ህብረተሰቡን በልማት እንዲክሱ የስራ እድሎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የሠላም ስምምነቱን ተከትሎ የገቡ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋሞ ተግባራት እየተከናወነ ነው ያሉት ደግሞ በብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የዲሞብላይዜሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ጎሳዬ ጥላሁን ናቸው።
ብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽኑ በአማራና በትግራይና ክልሎች በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና እንዲያልፉ በማድረግ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ 502ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል መካሻ ጀንበሬ በአማራ ክልል ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት የሰላም አማራጭ ተቀብለው ለመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የህዝብን ሰላም በማስቀደም ፣ቀጠናዊ ጉዳዮችን በመገምገምና የህዝቡን ስሜት በመረዳት ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረሱን የተናገሩት ደግሞ የታጣቂ ቡድኑ የቀድሞ አመራር የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ ናቸው።
የክልሉን ሠላም ለማናጋትና በህዝብ ላይ በደል የማድረስ ተልእኮ ያላቸው ቡድኖችን እንዲሁም የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ለማምከን ከመንግስት ጋር ተባብረው ለመስራት እንዳቀዱም ተናግረዋል።
የተሀድሶ ስልጠናውን ከተከታተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል አስር አለቃ አዳነ መሳፍንት በበኩላቸው የክልሉን ህዝብ ወደ ግጭት በማስገባት የበደሉትን ህዝብ በልማት ለመካስ መወሰናቸውን ተናግረዋል።
በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት የበደሉትን ህዝብ በልማት ለመካስ መዘጋጀታቸውን ያስረዱት ሌላው የቀድሞ ታጣቂ ቶማስ አያሌው ናቸው።
አሁን ላይ ከጥፋታቸው ተምረው መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ በመከተል ወደ መደበኛ ስራቸው ለመመለስ የተሀድሶ ስልጠና መውሰዳቸውን አንስተው ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ጫካ የቀሩ ወገኖችም እድሉን እንዲጠቀሙ መክረዋል።
በስነ ስርእቱ ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።