በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብቃት ያለው የሰው ሃይል የማፍራትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብቃት ያለው የሰው ሃይል የማፍራትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብቃት ያለው የሰው ሃይል የማፍራትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ዛሬ የክልሉ መንግስት በ60 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በፕሮፌሰር ገቢሳ እጄታ እናት ስም ተመርቆ ለማህበረሰቡ አገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የቢሮ ኃላፊው ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብቃት ያለው የሰው ሃይል የማፍራትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ቡኡራ ቦሩ በተሰኙ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለመማር ማስተማር ስራው መሰረታዊው ጉዳይ የትምህርት ቤቶች ደረጃን የማሻሻሉ ተግባርም መሆኑንም ገልጸዋል።
ትውልዱ በእውቀት ተመራምሮ ለሀገሩና ለዓለም ውጤት ለማስገኘት ጠንክሮ መማር እንዳለበት የገለጹት ደግሞ ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ ናቸው።
የተገነባው ትምህርት ቤት ለዚሁ አጋዥ መሆኑና በእናታቸው ስም መሰየሙ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም ትምህርት ቤቱን ይበልጥ በቴክኖሎጂ በማደራጀት የምርምርና የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እንደሚሰሩም ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ባንዲራ ጋላና፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና ያሉትን የማስፋፋት ስራዎች በሰፊው እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ መገንባት በአካባቢው የነበረውን የትምህርት ቤቶች እጥረት በመቅረፍ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ያስችላል ሲሉም አስረድተዋል።
ዛሬ የተመረቀው ትምህርት ቤትም የተማሪዎች መማሪያ ክፍል፣ የአስተዳደር ሕንፃና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎችም ኦሎንኮሚ ሞቱ አያኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢያቸው ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ልጆቻቸው ጥራት ያለው ትምህርት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ትምህርት ቤት በክልሉ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄርሳ ላፎ ወረዳ ሲሆን መታሰቢያነቱም ለእናታቸው ወይዘሮ ሞቱ አያኖ መሆኑ ታውቋል።