ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች ለማር ምርታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች ለማር ምርታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

የኢትዮጵያ ምቹ የአየር ጠባይና የአረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋን ዕድገት የበርካታ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አማካሪ ግርማ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የግብርና ምርታማነትን ማሻሻል መርሃ ግብሮች በማር ምርታማነት ላይ እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ነው።

በተለይም የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች የዜጎችን የንብ ማነብ ተነሳሽነት በማሳደግ በማር ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ውጤት አንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ የማር ምርታማነትም ዜጎች የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓት የሚያገኙበትን አማራጭ በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ጭምር እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የዜጎችን የንብ ማነብ የሥራ ባህል በማሳደግ የማር ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችል ምኅዳር የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

በማር ምርታማነት ለተመዘገበው ስኬትም የንብ አናቢዎች ዘመናዊ የአመራርት ዘዴ የግንዛቤ ማስጨበጫና የግብዓት አቅርቦት መሻሻል ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት 326ሺህ ሜትሪክ ቶን የማር ምርት በመሰብሰብ በተያዘው በጀት ዓመት 375 ሺህ ሜትሪክ ቶን የማር ምርት ለመሰብሰብ በተያዘው ዕቅድ መሠረት አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

የማር ምርት በጥራትና በብዛት በማምረት የውጭ ገበያ የማር ምርት አቅምን ለማሳደግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ ንብ ሃብት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ነጋሽ በቃና በበኩላቸው፤ መንግስት ለግብርና ምርታማነት የሰጠው ትኩረት በማር ምርታማነት ላይ ውጤት እንዲገኝ እያስቻለ ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሮችም በርካታ ዜጎች በንብ ማነብ የሥራ መስክ በመሰማራት የማር ምርታማነት ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የድርሻውን እንዲወጣ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም