በድሬዳዋ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከ48 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ስራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከ48 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ስራ ገብተዋል
ድሬዳዋ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ያለፉት ስድስት ወራት ከ48 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ስራ መግባታቸውን የንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የኮሪደር ልማትና መሠረተ ልማት ስራዎች የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ ናቸው።
በቢሮው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጥናት መረጃ ዝግጅት ቡድን መሪ አበራ መንግሥቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከ48 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 251 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል።
ፈቃድ ከወሰዱ አልሚዎች መካከል በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 10 የሚሆኑት ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውንና ለ1ሺህ 800 ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በግማሽ በጀት ዓመቱ ወደ ስራ የገቡ አልሚዎችም በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽንና በግብርና ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልጸው በዚህም ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።
እንደ አቶ አበራ ገለፃ ድሬዳዋ ለጅቡቲ ወደብ ያላት ቅርበት፣ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በፌዴራል እና በአስተዳደሩ ለባለሃብቶች የሚደረገው ድጋፍ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመር አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው።
እንዲሁም ባለፉት የለውጥ አመታት የተዘረጉ መሠረተ ልማቶች፣ የኮሪደር ልማት እና ነፃ የንግድ ቀጣናው ለኢንቨስትመንት ስራ የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች ልዩ ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ የመሬት ልማትና ማኔጀመንት ቢሮ ኃላፊ ሳጅድ አልይ ናቸው።
ባለሃብቶች የሚሰጣቸውን መሬት ለታለመለት አላማ በፍጥነት እንዲያውሉ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል።
የኤ ኤም ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያ ኢንዱስትሪ ስራ-አስኪያጅ አለማየሁ ሚደቅሳ፤ በተሰጣቸው ምቹ ቦታ የከባድ መኪና እና ለህዝብ ትራንስፖርት የሚውሉ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ለመገጣጠም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።