ያስተማራቸውን ማህበረሰብ ያልዘነጉ የቦረና ቅን ልቦች - ኢዜአ አማርኛ
ያስተማራቸውን ማህበረሰብ ያልዘነጉ የቦረና ቅን ልቦች
የሆስፒታሎችን የሕክምና ቁሳቁስ ፍላጎት በመገንዘብ አሳድጎ ያስተማራቸውን ማህበረሰብ ያልዘነጉ የቦረና ቅን ልቦች።
ዶክተር አብዱራህማን ሮኔ ይባላሉ። ትውልድና ዕድገታቸው በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ተልተሌ በተሰኘ አካባቢ ነው። የቀለም ትምህርት በሀገር ቤት ከተከታተሉ በኋላ ወደ ሀገረ አሜሪካ በማቅናት ኑሯቸውን በዚያው አድርገዋል።
ለበርካታ ዓመታት ሕይወታቸውን በአሜሪካን ሀገር እየመሩ የሚገኙት ዶክተር አብዱራህማን ከሁለት ዓመታት በፊት ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ቦረና አቀኑ። የጉዟቸው ዓላማ ለዓመታት የናፈቋቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ብቻ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በቤተሰብ ጥየቃ ቆይታቸውም በቦረና ዞን ተልተሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የሚጎበኙበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ጉብኝታቸውም ሆስፒታሉ በኪነ-ሕንፃ የተዋበ መሆኑን ነገር ግን የህክምና ግብዓት እጥረት ያለበት ሆኖ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
በተልተሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ምልከታቸው በሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ታካሚዎች ሲቸገሩ ማየታቸው የወቅቱ አሳዛኝ ትውስታ እንደነበርና ይህን እጥረት ወደ አሜሪካን ሀገር ሲመለሱ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው መወሰናቸውን አስታውሰዋል።
ዶክተር አብዱረሃማን በተልተሌ አካባቢ ተወልደውና አድገው ለሕክምና ባለሙያነት ያበቃቸውን ትምህርት የቀሰሙ ሰው በመሆናቸው በሆስፒታሉ የተመለከቱት የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት የሺዎችን ሕይወት የሚታደግ ሰብዓዊ ፕሮጀክት የሚቀረጽበት ሃሳብ እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል።
ከዚያም የራሳቸውን የሕክምና ሙያ ዕውቀትና በውጭ ያካበቱትን ግንኙነት በመጠቀም መነሻቸውን ባለፈው ዓመት ለተልተሌ እና ሜጋ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ዘመናዊ የሕክምና ቁሳቁስ በድጋፍ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም የሞያሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ጨምሮ ለሶስት ትላልቅ የጤና ተቋማት ዘመናዊ ሕክምና መሳሪያዎችን አበርክተዋል። እነኚህ የሕክምና መሳሪያዎች አሳድጎ ያስተማራቸውን ማህበረሰብ ያስታወሱበት በጎ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በማስታወስ መንግስት የዜጎችን የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላኛው በአሜሪካን ሀገር በሕክምና ሙያ የሚያገለግሉት ዶክተር ዋቆ ዳደቻ በበኩላቸው፤ ሁሉም ዜጋ በትብብር መስራት ከቻለ የማህበረሰብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ይቻላል ይላሉ።
ይህ የሆስፒታሎችን የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ለማሟላት የሚደረገውን ተሳትፎ ሁሉም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች ሊማሩበት የሚገባ በጎ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንግስት የሕክምና ተቋማትን ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ አሳድጎ ያስተማራቸውን ማህበረሰብ ማሰብ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ በውጭ የሚኖሩ የሕክምና ሙያተኞች የሚያደርጉት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በአርዓያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።
በዶክተር አብዱራህማን መሪነት ለቦረና አካባቢ ሆስፒታሎች የተደረገው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍም የተቋማቱን የጤና አገልግሎት ጥራት በማስጠበቅ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በመግለጽ።
በቀጣይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህዝባቸውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማገዝ በኩል የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።