ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን የውበት ልክና መልክ የሚያስተዋውቁ ናቸው - የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን የውበት ልክና መልክ የሚያስተዋውቁ መሆናቸውን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ጽዱ ለማድረግ የተገነቡ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ የልማት ሥራዎች መዲናዋን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ገጽታ አላብሰዋታል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገር፣ በሰው ተኮር፣ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች አዲስ አበባን የለውጥ ምሳሌ አድርገዋታል።


 

ይህም ለመዲናዋ ነዋሪዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ምቹ ገጽታ በማጎናጸፍ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል ተወዳዳሪነትን የገለጡ ሆነዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎችም፤ የአዲስ አበባ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስኬቶች ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ በማድረግ ምቹ የከተሜነት ምኅዳር የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ኢንጂነር ሳምሶን ወልደማሪያም እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ወንዞች ያጋጥማቸው የነበረው ብክለት ለነዋሪዎች የጤና መታወክ መንስኤ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህ መነሻነትም በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት የተገኙ የልማት ውጤቶች በመዲናዋ የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ ምቹ የከተሜነት ምኅዳር እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።

በመዲናዋ በሁሉም አካባቢዎች ጽዱና ምቹ የመዝናኛ ስፍራ መፈጠራቸው ነዋሪዎች የአዕምሮ እረፍት የሚያገኙበትን ዕድል እንደፈጠረ ተናግረዋል።

የወንዝ ዳርቻ እና መዲናዋን የማስዋብ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን ገናና የስልጣኔ ታሪክና ማንነት በልኩ በመግለጥ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የመዲናዋ ነዋሪ ዘሪሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ መንፈስን የሚያድስ የጥሞና ጊዜ ማሳለፊያ ምቹ የመዝናኛ ስፍራዎች ተፈጥረዋል ብለዋል።

የመዲናዋ ውብ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የጥበብ ስራዎቻቸውን መስራት የሚሹ ሙያተኞች በአቅራቢያቸው የሚሰሩበትን ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል።


 

ከተማዋ ሀገር ተረካቢ ለሆኑ ህፃናትም ምቹ የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጅታለች ያሉት ደግሞ ካዛንቺስ አካባቢ አካባቢ በሚገኘው የመዝናኛ ስፍራ ልጆቹን ሲያጫውቱ ያገኘናቸው ናትናኤል መላኩ ናቸው።

ህጻናትን ታሳቢ ያደረጉ የመዝናኛ ስፍራዎች ልማት መኖራቸው ልጆች ጤናቸው በሚጠበቅበትና ለአደጋ አጋላጭ ባልሆኑ ቦታዎች ጥሩ ጊዜ ከቤተሰብ ጋር እንዲያሳልፉ ያደርጋል ነው ያሉት።


 

አቶ አብነት ሹምባሽ በበኩላቸው ይህ አስደናቂ ልማት የዜጎችን ጤና ከማስጠበቅ ባለፈ እንደ አፍሪካ መዲናነት የኢትዮጵያን መልክና ውበት በሚገባ የሚያስተዋውቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም