ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የተዘረጉ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥና የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እያጎለበቱ መጥተዋል

ሐረር ፤ጥር 17/2018(ኢዜአ)፡-  በሐረሪ ክልል የተዘረጉ ቀልጣፋ  የአገልግሎት አሰጣጥና የልማት ስራዎች  የህዝቡን ተጠቃሚነት እያጎለበቱ  መምጣታቸውን  ነዋሪዎች ተናገሩ።

የህዝቡን የልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባራት በቅንጅት በማከናወን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሃብት ቢሮ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ህዝባዊ መድረክ አካሂዷል።


 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ የተከናወኑ የልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ   ጠይቀዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ኡስማን ዩስፍ እንዳሉት በክልሉ ህዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የነዋሪውን ተጠቃሚነት እያጎለበቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ የተከናወኑ እንደ ኮሪደር ልማት ስራዎች እና ሌሎች ልማቶች  የህዝቡን ጥያቄ የመለሱ በመሆኑ  እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።

የነዋሪው ጥያቄ የነበሩ  የመንገድና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መፍትሄ አግኝተዋል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋንቱ እሸቱ ናቸው።


 

ከተማዋን ውብ እና ለጎብኚውም ሆነ ለነዋሪዎች  ምቹ በማድረግ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር በማድረጉ ለስራ እድል ፈጠራና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እየተሳለጡ መሆናቸውን  ያወሱት ደግሞ  ሻምበል ጋሻው ሙሉዓለም ናቸው።

ይህም ተግባር የክልሉ አመራርና የህዝብ ቅንጅት ውጤት በመሆኑ በቀጣይም በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና  የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ ነጋዴዎችን መቆጣጠር ላይ መጠናከር እንዳለበት  ጠይቀዋል።


 

በክልሉ በማህበረሰብ ጤና መድህን እየተከናወነ የሚገኘው ስራ አቅመ ደካሞችን እያገዘ መሆኑንና በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥም  ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፋቸው ሊበረታቱ ይገባል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሳራ ይስሃቅ ናቸው።


 

በቀጣይም ያልተገባ ዋጋ በሸቀጦች ላይ በመጨመር ህዝቡን ለምሬት እየዳረጉ የሚገኙትን ስግብግብ ነጋዴዎችን የሚወሰደው  ቁጥጥር  እንዲጠናክር  አመልክተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ህዝቡ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ከልማት ተደራሽነትና ከኑሮ ውድነት ጋር ያነሳው ሃሳብን በዕቅድ በመያዝ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል። 

የማህበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የልማት ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የዋጋ ግሽበትን ለመቅረፍ ምርታማነትን ማሳደግና ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም