ቀጥታ፡

በክፍለ ከተማው የእንስሳት እርባታ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርና ለገበያ ማረጋጋት እያገዘ ነው

ሸገር ፤ጥር 17/2018 (ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ የእንስሳት እርባታ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርና ለገበያ ማረጋጋት  እያገዘ ነው።

በፉሪ ክፍለ ከተማ ሙዳ ወረዳ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች  መካከል ቱሬ ቦሩ አምስት ሆነው  በወተት ልማት በመደራጀት  ተጠቃሚነታቸውን  ማሳደጋቸውን ገልጿል።

ለስራው ውጤታማነትም  የመንግስት የመስሪያ ቦታ መስጠትና፣ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት እንዲሁም  የስልጠና አገልግሎት እንዳገዛቸው ተናግሯል።

የወተት ልማት ስራው በማደጉም በቀን በአማካኝ እስከ 110 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን  ከማረጋገጥ አልፈው  ለሌሎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።


 

ሌላው የዚሁ ወረዳ ወጣት ሂንሰርሙ ፍቃዱ  በበኩሉ በወተት ልማት ማህበር ስድስት ሆነው በመደራጀት   በጀመሩት ስራ  በቀን ከ100 ሊትር በላይ ወተት ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።

በገቢውም  ራሳቸውን ከመለወጥ አልፈው ለሌሎች ሰዎችም የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

በዚሁ የወተት ልማት ማህበር ተቀጥረው የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ሰዎች  መካከል አቶ ተስፋዬ ተረፈ እንዳሉት  በማህበሩ  ተቀጥረው ከሚያገኙት ወርሃዊ ደሞዝ በተጓዳኝ  በዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ልምድ እንዳገኙ  ገልጸዋል።   


 

በከተማ አስተዳደሩ የፉሪ ክፍለ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞቱማ ጉተታ እንደተናገሩት በክፍለ ከተማው  ግብርናን በማዘመን ምርታማነቱን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ  ተችሏል። 


 

ከዚህ በተጓዳኝ ስራ አጥ ወጣቶቹን በማደራጀት በተለያዩ የስራ መስክ ለማሰማራት በክላስተር ደረጃ 329፣ በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ 378  ሼዶች መተላለፋቸውን  ተናግረዋል።

በዚህም  በወተት ላሞች እርባታ፣በከብት ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብና በአሳ ምርት  በርካታ ዜጎች ተደራጅተው  የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የስራ እድሉ ተጠቃሚዎችን ውጤታማ ለማድረግም  የቦታ አቅርቦትና  ከሲንቄ ባንክ ጋር በማስተሳሰር  ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መቅረቡን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም የስልጠናና የባለሙያ ድጋፍና ክትትልም፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦትና የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው አንስተዋል።


 

በፉሪ ክፍለ ከተማ የሙዳ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ነጌሶ ደሜ በበኩላቸው በወረዳው  ስራ አጥነትን  ለመቅረፍ ዜጎች በእንስሳት እርባታ ዘርፍ  ተደራጅተው  ውጤታማ   እንዲሆኑ   እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም 128 ሼዶችን   በማቅረብና  የብድር አቅርቦትን በማመቻቸት ለወጣቶች የስራ እድል  መፍጠር  መቻሉን  አስረድተዋል።

የእስሳት እርባታው  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና  ገበያን ለማረጋጋት  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም