ቀጥታ፡

የቀድሞ የኢዜአ ጋዜጠኛ ደባልቀው ይርዳው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፡- የቀድሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ ደባልቀው ይርዳው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ደባልቀው የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ እና ስነጽሁፍ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን አጠናቀዋል፡፡

የጋዜጠኝነት ህይወታቸውንም በሀረር የኢዜአ ዋና ወኪል ሆነው መጀመራቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ጋዜጠኛ ደባልቀው ወደ ኢዜአ ዋና መስሪያ ቤት በመዘዋወርም ከሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት አገልግለዋል፡፡

ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስም በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የፕሮቶኮል ቡድን መሪ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ደባልቀው ባለ ትዳርና የአንድ ልጅ አባት ሲሆኑ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአቶ ደባልቀው ይርዳው ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡

የጋዜጠኛ ደባልቀው የቀብር ስነስረዓት ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ30 በመርሀቤቴ ፌጥራ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ይፈጸማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም