የጊፋታ በዓል በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የጊፋታ በዓል በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ፈጥሯል
ወላይታ ሶዶ: ጥር 17/2018(ኢዜአ):- የጊፋታ በዓል በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት መፍጠሩን የወላይታ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
የጊፋታ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን አስመልክቶ "የጊፋታ ብስራቶች ለህዝባችን ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ የማስ ስፖርትና የሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ባስተላለፉት መልዕክት ጊፋታ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ለአካባቢው ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል።
በዞኑ የባህል እሴቶችንና የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት መሰራቱን ተናግረዋል።
የዚሁ አካል የሆነው የጊፋታ በአልን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በተደረገው ጥረት የሚታይ ውጤት እንደተመዘገበበት ጠቅሰዋል።
የጊፋታ ሩጫ የባህል እሴቱን ጠብቆ ከማቆየት ባለፈ ለልማት ለማዋል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስሞኦን ስላሎ ናቸው።
ጊፋታ በዩኔስኮ መመዝገቡ በዘርፉ እያመጣ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል በቅንጅት መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካካል አቶ አጥናፉ ሶዳኖ ሩጫው ወላይታንና ጊፋታን ለዓለም በማስተዋወቅ ለቀጣይ ትውልድ የሚሻገር አሻራ ለማሳረፍ አበርክቶው የጎላ በመሆኑ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሪት የምስራች አስራት በበኩላቸው ጊፋታ በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ የተደረገው ሩጫ ባህሉን ለዓለም ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በሚቀጥለው ጊዜም ጊፋታንና እሴቶቹን ለታናናሾቼ በማስተዋወቅ አሻራዬን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነኝ ብላለች።
በዕለቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን በሩጫው ላሸነፉ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።