ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ባህር ዳር ከተማ ከሃዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል። 

ምሽት 12 ሰዓት ባህር ዳር ከተማ ከሃዋሳ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ባህር ዳር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን 16 ጨዋታዎችን አድርጎ በአራቱ ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል። ዘጠኝ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 11 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ21 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። 

ባህር ዳር ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በርካታ ጨዋታዎችን አቻ የወጣ ቡድን ነው።

ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ ካከናወናቸው 16 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 18 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ሃዋሳ ከተማ በ28 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ሃዋሳ ከተማ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል። 

ባህር ዳር ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

በሌላኛው መርሐ-ግብር አርባምንጭ ከተማ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ ያላሸነፈ ብቸኛው ቡድን ነው። በስምንት ጨዋታዎች ሲሸነፍ በተመሳሳይ ስምንት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አምስት ግቦችን ሲያገባ 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።  

ቡድኑ በስምንት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል። 

በውድድር ዓመቱ ካካሄዳቸው 15 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው ፋሲል ከነማ በበኩሉ አንድ ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 10 ግቦችን በ15ቱ ጨዋታ ላይ ሲያስቆጥር አምስት ግቦችን አስተናግዷል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከነማ በ26 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። 

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት ይጫወታል። ፋሲል ከነማ ማሸነፍ ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት እንዲመለስ ያደርገዋል።

አዳማ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አዳማ ከተማ በ26 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። መቀሌ 70 እንደርታ በ16 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።

ከቀኑ 7 ሰዓት ሀዲያ ሆሳዕና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ሀዲያ ሆሳዕና በ20 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ13 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ማሸነፍ ወደ ድል ይመልሰዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል። 

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ33 ነጥብ እየመራ ነው።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በተመሳሳይ ስምንት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም