ለሰላም ህዝቡና መንግስት አበክረው በመስራታቸው መልካም ውጤት መጥቷል - የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ህዝቡና መንግስት አበክረው በመስራታቸው መልካም ውጤት መጥቷል - የሀገር ሽማግሌዎች
ወልዲያ፤ ጥር 17/2018 (ኢዜአ)፡-ለሰላም ግንባታ ህዝቡና መንግስት አበክረው በመስራታቸው መልካም ውጤት መገኘቱን የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በጥፋታቸው በመፀፀት ትጥቃቸውን በማስረከብ የበደሉትን ህዝብ በስራ ለመካስ የመጡ ታጣቂዎች የሰላም ጀግኖች በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋልም ብለዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በተለይም የአማራ ክልል መንግስት እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) የዘላቂ ሰላም ስምምነት በማድረጋቸው በተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ማስረከባቸውን ቀጥለዋል።
የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድና በዘላቂነት የማቋቋም እድሉ ተጠቃሚ በመሆን ለሰላምና ልማት በመሰለፍ እየሰሩም ይገኛሉ።
በመሆኑም በክልሉ እየተደረገ ያለውን የሰላም ጥረትና የመጣውን ውጤት በማስመልከት የኢዜአ ሪፖርተር በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማና በአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል።
ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ አለነ ከበደ፤ በአካባቢው ቀደም ሲል በነበረው የጸጥታ መደፍረስ በነዋሪዎች ዘንድ ብዙ ችግሮች ስለመድረሳቸው አስታውሰዋል።
የግጭትና አለመረጋጋት ውጤቱ ጥፋት እንጂ ምንም አይነት ጥቅም የሌለው መሆኑን አንስተው ለሰላም ግንባታ ህዝቡና መንግስት አበክረው በመስራታቸው መልካም ውጤት መጥቷል ብለዋል።
ለመንግስት የሰላም ጥሪ ቀና ምላሽ የሰጡ ወገኖችም ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችም ተጨማሪ ህይወትና ንብረት እንዳይጠፋ የሰላም ጀግኞች ሆነው በመገኘታቸው ሊከበሩ ይገባል ብለዋል።
ሌሎች ታጣቂዎችም የወንድሞቻቸውን ፈለግ በመከተል ጊዜ ሳይወስዱ ወደ ሠላም መድረክ እንዲመለሱ አባታዊ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
ለበርካታ ጊዜ ስንደክምበት የነበረው የሠላም ጥሪ አሁን ላይ የሚታይ ውጤት እያመጣ በመሆኑ በሁላችንም ዘንድ ደስታ ፈጥሯል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ በላይ ገላው ናቸው።
በዚህ ረገድ የመንግስት ያላሰለሰ የሰላም ጥረት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን አንስተው ጥሪውን ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችም አርአያነት ያለው ተግባር ፈፅመዋል ብለዋል።
አሁንም ቢሆን በጫካ የቀሩ ወገኖች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ሳይውሉ ሳያድሩ እንዲመጡ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሌላው የአገር ሽማግሌ አቶ ሲሳይ ጸጋዬ፤ የሽምግልና ጥረት አንድ ጊዜ ተሞክሮ የሚቆም ሳይሆን ችግሩ እልባት እስኪያገኝ የሚቀጥል መሆኑን አንስተው የመንግስትም ጠንካራ ጥረት ታክሎበት ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም በየመድረኮቹ ስናነሳው የነበረው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ፍሬ አፍርቶ በማየታችን ተደስተናል በማለት በቀጣይም ለዘላቂ ሰላምና ልማት ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።