በምርጫው በሃሳብና በፖሊሲ አማራጮች ላይ ተከራክረን ሰላማዊ ፉክክር ለማድረግ ተዘጋጅተናል - የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው በሃሳብና በፖሊሲ አማራጮች ላይ ተከራክረን ሰላማዊ ፉክክር ለማድረግ ተዘጋጅተናል - የፖለቲካ ፓርቲዎች
ቦንጋ፣ ጥር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ በሃሳብና በፖሊሲ አማራጮች ላይ ተከራክረው ሰላማዊ ፉክክር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሂድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ከዚህም በመነሳት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው የህዝብን ድምጽ ለማግኘት ከወዲሁ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ኢዜአ የምርጫ ዝግጅታቸውን በተመለከተ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን አነጋግሯል።
ከፓርቲዎቹ አመራሮች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ(ኢብአፓ) ሰብሳቢ መቅደስ መኮንን፤ ፓርቲያቸው ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት አባሎቹንና ደጋፊዎችን በማንቃት ለፉክክሩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በምርጫው ሀሳብ ይዞ በመቅረብና በፖሊሲ አማራጮች ላይ ክርክርና ፉክክር በማድረግ የህዝብ ይሁንታ ማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ አመራርና የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፀሐፊ ሰለሞን መኮንን እንዳሉት፤ ፓርቲያቸው ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው።
ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት አባላትና ደጋፊዎቹ የሚጠበቅባቸውን ግዴታና ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጋራ ምክር ቤቱ የሚገኙ ሁሉም ፓርቲዎች ለምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የበኩላቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት(ካህዴህ) ፓርቲ ሰብሳቢ ቦጋለ ኃይሌ በበኩላቸው ፓርቲያቸው የተሻለ ሀሳብና የፖሊሲ አማራጭ በመያዝ በምርጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዚህ በኩል ፓርቲያቸው ለአባላቱ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።