የታሪካዊ ተቀናቃኞቹ አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ የዛሬ ምሽት ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
የታሪካዊ ተቀናቃኞቹ አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ የዛሬ ምሽት ፍልሚያ
አዲስ አበባ፤ ጥር 17 /2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 በኤምሬትስ ስታዲየም ይደረጋል።
አርሰናል በሊጉ ባደረጋቸው 22 ጨዋታዎች 15 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 5 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
መድፈኞቹ በጨዋታዎቹ 40 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፉ 14 ግቦችን አስተናግደዋል።
በ43 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ የሚመራው አርሰናል በ50 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ማንችስተር ዩናይትድ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 22 ጨዋታዎች 9 ጊዜ ሲያሸንፍ 5 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪዎቹ 8 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።
ቀያዮቹ ሴይጣኖች 38 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 32 ግቦችን አስተናግደዋል።
በ44 ዓመቱ እንግሊዛዊ ማይክል ካሪክ የሚሰለጥነው ማንችስተር ዩናይትድ በ35 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ246ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በነበራቸው 245 የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ማንችስተር ዩናይትድ 99 ጊዜ አሸንፏል።
አርሰናል 91 ጊዜ ሲያሸንፍ 55 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ 66 ጊዜ ተጫውተዋል። ማንችስተር ዩናይትድ 25 ጊዜ ሲያሸንፍ አርሰናል በ23ቱ ድል ቀንቶታል። 18 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አርሰናል አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።
ዩናይትድ በሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ አርሰናልን ያሸነፈው እ.አ.አ ሴፕቴምበር 4 2022 ሲሆን በወቅቱ የ 3 ለ 1 ድል ተቀዳጅቷል።
አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪካዊ ተቀናቃኞች የሚባሉ ቡድኖች ናቸው።
ክለቦቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1894 ነበር። በዚሁ ጨዋታ ቡድኖቹ ሶስት አቻ ተለያይተዋል።
ቡድኖቹ ከመጀመሪያ ጨዋታቸው አንስቶ ለ131 ዓመታት የቆየ ፉክክር በእንግሊዝ እና በአውሮፓ መድረክ አድርገዋል።
አርሰናል የሊጉን ዋንጫ 13 ጊዜ ሲያነሳ ማንችስተር ዩናይትድ 20 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
ጨዋታው አርሰናል ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፤ ዩናይትድ ከማንችስተር ደርቢ ድል በኋላ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።
የ41 ዓመቱ ክሬግ ፓውሰን የሁለቱን ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ክሪስታል ፓላስ ከቼልሲ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከአስቶንቪላ እና ብሬንትፎርድ ከኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።