በክልሉ ለሰላም ግንባታ እና ለልማት ስራዎች የተሰጠው ትኩረት፣ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገትና ማንሰራራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለሰላም ግንባታ እና ለልማት ስራዎች የተሰጠው ትኩረት፣ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገትና ማንሰራራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
ባህር ዳር፤ ጥር 17/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ለሰላም ግንባታ እና ለልማት ስራዎች የተሰጠው ትኩረት፣ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገትና ማንሰራራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት በክልሉ ከዘርፉ ከ7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ መገኘቱንም አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራባቸው ከሚገኙትና ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው።
የመደመር መንግስት በኢትዮጵያ ያለውን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ መለየት፣ ማልማትና መጠቀም ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በገበታ ፕሮጀክቶች የተገበራቸው የቱሪዝም ልማቶች በዘርፉ ዕድገት ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥረዋል።
የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ መልካሙ ጸጋዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በክልሉ በመጣው የተረጋጋ ሰላም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች የቱሪዝም መስህቦችን ለመጎብኘት እንዲመጡ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
በክልሉ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የአደባባይ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር መከበራቸውን ጠቅሰው፣ ተቀዛቅዞ የቆየው የቱሪዝም ዘርፍ በእነዚህ በዓላት መነቃቃቱን አመልክተዋል።
በመሆኑም በክልሉ ለሰላም ግንባታና ለልማት ስራዎች የተሰጠው ትኩረት፣ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገትና ማንሰራራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ቱሪስቶች የክልሉን የመስህብ ሥፍራዎች መጎብኘታቸውን አመልክተው፣ ከእነዚህ ውስጥ 24 ሺህ የሚሆኑት የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም የጥምቀት በዓልን ሳያካትት ከ7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።
በክልሉ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት፣ የፋሲል አብያተ መንግስታት ጥገና እና የሌሎች ቅርሶች ጥገና፣ ጥበቃና እንክብከቤ የቱሪስቶችን ቀልብ እየሳበ መምጣቱን አመልክተዋል።
እንዲሁም ለጎብኚዎች እየተሰጠ ያለው ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ ከፍ እንዲል ማድረጉን አብራርተዋል።
ቀደም ሲል የነበረው አማካይ የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት እንደነበረ አንስተው፤ አሁን ላይ ወደ አምስት ቀናት ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል ክልሉ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እንዲዘልቅ የ25 ዓመት የልማት ዕቅድና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን አመልከተዋል።