ቀጥታ፡

ሀገር በቀል የፍትሕ ሥርዓቶችን ማዘመን ለፍትሕ ተደራሽነትና ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገር በቀል የፍትሕ ሥርዓቶችን ማዘመን ለፍትሕ ተደራሽነትና ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋራ ትብብር የተዘጋጀው “የሕግ የበላይነትና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች - ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በባህር ዳር በመካሄድ ላይ ነው።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም፣ ለዕድገትና ኢንቨስትመንት መሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

እንደ ሽምግልና ያሉ ሀገር በቀል ሥርዓቶች በመግባባትና ማኅበረሰባዊ ሰላምን በመፍጠር ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ለውስብስብ ችግሮች ቅቡልነት ያለው መፍትሔ እንደሚያመጡም ጠቁመዋል።

መደበኛው ፍርድ ቤት በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንደሚያተኩር በመጥቀስ፣ ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች ግን እስከ ዘላቂ ዕርቅና ማኅበራዊ መስተጋብር ድረስ እንደሚዘልቁ አስረድተዋል።

በሀገራችን ብሎም በአማራ ክልል የሚተገበሩ ሀገር በቀል የፍትሕ አሠራሮች በትክክል ጥቅም ላይ ከዋሉ በመደበኛ የፍትሕ ተቋማት ላይ ያለውን ከፍተኛ የሥራ ጫና ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚያቃልሉና በማኅበረሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ያላቸው መፍትሔዎችን እንደሚያቀርቡም አስገንዝበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የድህነት ፈተናዎች፣ ግጭቶች፣ ክርክሮች እና ያለመግባባቶች መደራረብ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን እንደፈተኗቸው አንስተዋል።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በተለያዩ ፖለቲካዊ እና ግላዊ ምክንያቶች መሣሪያ ያነሡ አካላት፣ ባህላዊውንም ሆነ መደበኛውን የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዳከም ሆን ብለው ሠርተዋል ነው ያሉት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽና በመርሕ ላይ የቆመ ፍትሕን ለማስፈን ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን ከዘመናዊ ዕሳቤዎችና ከሀገራዊ ሪፎርሙ ጋር ማጣጣም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሀገር በቀል ተቋማትን አሠራር በሕግ በመደገፍና በማዘመን ተቋማዊ ቁመና እንዲኖራቸው ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በመደበኛና በባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች መካከል በተናበበ መልኩ የሚሠራበትን ዐውድ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸው፤ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ባህላዊና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎችን በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በቋሚነት ማዋቀር ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የግልግልና የዕርቅ ሥርዓት ሕግ እንዲሁም በአማራ ክልል የጸደቀው የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ ዐዋጅ ለፍትሕ ዘርፉ ተቋማዊና ዘመናዊ ቁመና ማጎናጸፋቸውን ገልጸዋል።

አማራጭ የሙግትና የክርክር መፍቻ ሥርዓቶችን ማጠናከር በድኅረ-ግጭት ዐውድ ዕርቅ ለማስፈን፣ የተሰበሩ ግንኙነቶችን ለመጠገንና ውይይትን ከቅራኔ ለማስቀደም ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የመደመር መንግሥት የትላንት በጎ እሴቶችን ከዛሬ አዳዲስ እሴቶች ጋር በማጣመር ነገን የመገንባት ጽኑ እምነት አለው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ የባህላዊና የመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቶች አዎንታዊ ጥምረት እንደሚያስፈልጋት አስረድተዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም