ከቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተጨማሪ በንግድ ትርኢት እና ባዛርም ምርቶች እየቀረቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተጨማሪ በንግድ ትርኢት እና ባዛርም ምርቶች እየቀረቡ ነው
ጅማ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- በጅማ ከተማ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ከማስፋፋት ባለፈ በሚዘጋጁ የንግድ ትርኢት እና ባዛሮች ነዋሪው ምርትና ሸቀጦችን በአንድ ቦታ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው።
በጅማ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተዘጋጀ 15ኛ ዙር የንግድ ትርኢት እና ባዛር የተከፈተ ሲሆን፤ በባዛሩ ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ200 በላይ ነጋዴዎችና አምራቾች ተሳትፈዋል።
የጅማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ነጂብ ከድር በዚሁ ወቅት፤ የከተማው ነዋሪ በርካታ የገበያ አማራጭ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው።
ዛሬ በከተማው የተከፈተው የንግድ ትርኢት እና ባዛርም ነዋሪው በአንድ ስፍራ ምርት እና ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
የጅማ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉተማ ጊዲ በበኩላቸው፤ በከተማው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል አማራጭ ገበያ የማስፋት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም በከተማው የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማስፋት ሻጭ እና ሸማቹን አንድ ላይ ማገናኘት መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም ህገ ወጥ ደላሎች የሚፈጥሩትን ሰው ሰራሽ ችግር ማስወገድ አስችሏል ብለዋል።
ከቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተጨማሪ በተለይ በዓላትና የተለያዩ ሁነቶችን መነሻ በማድረግ የንግድና ትርኢት ባዛሮች እንዲዘጋጁ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።