የግብርና ልማት ኢንሼቲቮችን ለማሳካት ዘርፉን በሎጂስቲክ የመደገፍ ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ልማት ኢንሼቲቮችን ለማሳካት ዘርፉን በሎጂስቲክ የመደገፍ ሥራ ይጠናከራል
ሞጆ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል እየተተገበሩ ያሉ የግብርና ልማት ኢንሼቲቮችን ለማሳካት ዘርፉን በሎጂስቲክ የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ ገለፁ።
ቢሮው የክልሉን የግብርና ዘርፍ በሎጂስቲክስ ለመደገፍ የሚያግዙ 795 ሞተር ብስክሌቶችና 73 ተሽከርካሪዎችን ዛሬ ለተለያዩ ወረዳዎች አስረክቧል።
አቶ ጌቱ ገመቹ በርክክብ መርሐ-ግብሩ ላይ፤ የሞተር ብስክሌቶቹና ተሽከርካሪዎቹ በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ አካባቢ የግብርና ልማትን ለማፋጠን የሚከናወኑ ሥራዎችን እንደሚያግዙ ገልጸዋል።
በክልሉ የግብርና ሴክተሩን ለማዘመንና ለማሻገር የተለያዩ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት መኖ ልማት ኢንሼቲቮች ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆኑንም አብራርተዋል።
ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም ከምርት ማሳደጊያ ግብዓት አቅርቦት በተጨማሪ በሎጂስቲክስ ለማገዝ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶአደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየቀረበ መሆኑን እና በዚህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሠራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት የመስኖ ፕሮጀክቶችን ከማስፋፋት ባለፈ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የበጋ ስንዴን ጨምሮ የመስኖ ልማት በስፋት እንዲከናወን እያደረገ ይገኛል።
በዚህም በዘላቂነት ከተረጂነት ለመውጣት በርብርብ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የቢሮው ምክትልና የሰብል ልማት ዘርፍ ኃላፊ በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው፤ መንግሥት የክልሉን የግብርና ልማት ለማሻገር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
ተሽከርካሪዎችና ሞተር ብስክሌቶቹ በአርሶአደሩና አርብቶአደሩ አካባቢ ላሉ 72 ወረዳዎችና ለሸገር ከተማ አስተዳደር መሰጠታቸውንም ገልጸዋል።