የኤ ኤም ጂ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር የሚያገናኘው የባቡር መስመር ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኤ ኤም ጂ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር የሚያገናኘው የባቡር መስመር ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2018(ኢዜአ)፦ የኤ ኤም ጂ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የሚያገናኘው የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ማጠናቀቅ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኢትዮ-ጁቡቲ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ገለጸ፡፡
የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን አቅም መከናወኑ በቀጣይ በዘርፉ ለሚከናወኑ ሥራዎች የተሻለ ልምድና አቅም መፍጠር የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ኤ ኤም ጂ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከዋናው ኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር ጋር የሚያገናኘው የሶስት ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ግንባታ በመስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል፡፡
የባቡር መስመሩ መገንባት የባቡር መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የተለያዩ የወጭና ገቢ ምርቶችን ለማጓጓዝ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡
በኢትዮ-ጁቡቲ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ባለሙያዎች አቅም የሚገነባው ይሄው የባቡር መስመር ግንባታ በስድስት ወራት ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለታል፡፡
የፕሮጀክቱ ማናጀር ኢንጅነር ንግስት ሀይሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የባቡር መስመሩን ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ማጠናቀቅ የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት የባቡሩን ሀዲድ ለማንጠፍ የሚያስችሉ የጉድጓድ ሙሌት፣ የአፈር ቆረጣና ሙሌት እንዲሁም የማፋሰሻ ግንባታዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የባቡር መስመር ግንባታው 70 በመቶ መድረሱን ገልጸው፤ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችል አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የባቡር መስመር ግንባታው በኢትዮጵያውያን አቅም የሚሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አስፈላጊውን የሰው ሀይልና የግንባታ ግብዓቶች በማሟላት በትጋት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ግንባታው በኢትዮጵያውያን አቅም መሰራቱ በቀጣይ በዘርፉ ለሚከናወኑ ሥራዎች የተሻለ የሥራ ልምድና አቅም መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡