ኢኒስቲትዩቱ ይፋ ያደረገው የእንሰት መፋቂያ ቴክኖሎጂ የሥራ ጫናን ከማቅለል ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ኢኒስቲትዩቱ ይፋ ያደረገው የእንሰት መፋቂያ ቴክኖሎጂ የሥራ ጫናን ከማቅለል ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል
ሀዋሳ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፦የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ጋር በመቀናጀት ይፋ ያደረገው የእንሰት መፋቂያ ቴክኖሎጂ የሥራ ጫናን ከማቃለል ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሲዳማ ክልል ደቡባዊ ሲዳማ ዞን አለታ ወንዶ ወረዳ በኢንስቲትዩቱ የተሰራ ዘመናዊ የእንሰት መፋቂያ ቴክኖሎጂ ሽግግር ስራን ተመልክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺ ሀሰን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፣ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያቃልሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እያፈለቀ ይገኛል።
ከእነዚህ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የስራ ጫና የሚያቃልል የእንሰት መፋቂያ፣ መጭመቂያና መቁረጫ መሳሪያ አንዱ ነው ብለዋል።
በርካታ ሴቶች በእንሰት ሥራ እንደሚሰማሩ ገልጸው፣ እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች መምጣታቸው የሥራ ጫናውን ከማቃለል ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።