ገበያ ተኮር የግብርና ምርቶችን በብዛት የማምራት ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ገበያ ተኮር የግብርና ምርቶችን በብዛት የማምራት ሥራ እየተከናወነ ነው
አዳማ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርቶችን በጥራት እና በብዛት የማምራት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ተናገሩ።
በክልሉ የግብርና ሽግግር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የሁለተኛ ምዕራፍ የትግበራ ፕሮግራም ለባለድርሻ አካላት የማስተዋወቂያ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
አቶ አወሉ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፤ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተቀናጀ ቴክኖሎጂና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለአርሶአደሩ በአግባቡ ተደራሽ እየተደረገ ነው።
ሁለተኛው ምዕራፍ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ፕሮግራም በተለይም አርሶአደሩ የቴክኖሎጂና የግብዓት አቅርቦት በሚፈልገው መልኩ እንዲያገኝ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የእርሻ ትራክተርና ኮምባይነር በአግባቡ ማቅረብ እንዲቻል ሥራውን የሚያሳልጥ ኩባንያ እንደሚቋቋምም አመላክተዋል።
በብዛት ከማምረትና በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ገበያ ተኮር የግብርና ምርቶች በማምረት ለውጪ ገበያ የማቅረብ ሥራው እንደሚጠናከር አስገንዝበዋል።
አርሶ አደሩን ጨምሮ የግብርና ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በጥራት፣ በብዛትና በአይነት ማምረት ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ደሳለኝ ዱጉማ በበኩላቸው፤ በክልሉ በ25 የግብርና የምርት አይነቶች ምርታማነት ለመጨመር ኢንሼቲቭ ተቀርጾ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በክልሉ ከ7 ሚሊየን በላይ አርሶአደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው ወጥነት ባለው መልኩ ቴክኖሎጂና የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በተለይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ኢንዱስትሪ መር የግብርና አሰራርና አመራረት ሂደት ለመከተል እንዲሁም የአርሶአደሩን ተጠቃሚነትና የግብርና ሽግግር ለማፋጠን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወነ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም የሰብል እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ማሳደግ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
በዋና ዋና ሰብሎች በተለይ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ በቆሎና ሌሎች ሰብሎች ምርት ከመጨመር ባለፈ ከውጭ ሲገባ የነበረውን የስንዴና ቢራ ገብስ ምርት በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉንም አስታውሰዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ትግበራም ገበያ ተኮር የሰብል እና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በጥራት፣ በብዛትና በአይነት በማምረት በእሴት ሰንሰለት አልፈው ለገበያ እንዲቀርቡ ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም የምርት ማቀነባበሪያዎች በማስፋፋት ረገድ አርሶ አደሩ ባለቤት እንዲሆንና ለምርቱ ተገቢውን ገበያ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል።