ቀጥታ፡

የሴፍትኔት ፕሮግራሙ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ የሚቻልበትን ዕድል ፈጥሯል

አዳማ፣ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የምግብ ዋስትናና የሴፍትኔት ፕሮግራም ዜጎች ከራስ አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማስቻሉን የአዳማ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በአስተዳደሩ በምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በመሳተፍ ሽግግር ያደረጉ 646 አባወራና እማወራዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ንጋቱ ሞቱማ በዚሁ ወቅት፤ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ድህነትን በመቀነስና የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በከተማ ጽዳትና ውበት፣ በአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ላይ በመሳተፍ የራሳቸውን ገቢ በመፍጠር ኑሯቸውን አሻሽለዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ በከተማዋ በድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎችን ኑሮ በመቀየር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስተዳደሩ ተጠቃሚዎቹን ወደ ዘላቂ ልማት በማሸጋገር ረገድ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

አስተዳደሩ ለሥራ እድል ፈጠራ የገነባቸውን ሼዶች የፕሮግራሙ ተሳታፊዎችን በማደራጀት አንደሚያስተላልፍና የባንክ ብድር የሚያገኙበትን ዕድል አንደሚፈጥርምአመልክተዋል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ግዛው በበኩላቸው፤ በከተማዋ በተመረጡ አካባቢዎች የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ መተግበሩን አውስተዋል።

የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ከጊዜያዊ ድጋፍ ባለፈ ከተረጅነት ራሳቸውን በማላቀቅ ቋሚ ጥሪት ማፍራት እንዲችሉ የመቋቋሚያ ድጋፍ እንደተደረገላቸውም አረጋግጠዋል።


 

ከተጠቃሚዎች መካከል የመልካ-አዳማ ወረዳ ነዋሪ ዓባይነሽ ደርቤ፣ በፕሮግራሙ ከመታቀፋቸው በፊት ከአራት ልጆቻቸው ጋር በችግር ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።

በከተማ ጽዳትና ውበት ስራ በመሳተፍ ከሚያገኙት ገቢ ቆጥበው የወተት ላም በመግዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሪት ማፍራትና ኑሯቸውን ማሻሻል መቻላቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም