ቀጥታ፡

በፓርቲው መዋቅሮች ወጥነት ያለው ዘመናዊ አሠራር ለመዘርጋት የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሐዋሳ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ )፡- በብልጽግና ፓርቲ መዋቅሮች ወጥነት ያለው ዘመናዊ አሠራር ለመዘርጋት የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ስትራቴጂክ ሥራ አመራርና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ገለጹ።

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ስትራቴጂክ ሥራ አመራርና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ አዘጋጅነት ለዋና ጽሕፈት ቤትና ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አመራርና ባለሙያዎች በሐዋሳ ከተማ ሲሰጥ የቆየው የተቀናጀ የተቋም ሀብት አሥተዳደር አውቶሜሽን ትግበራ ሥልጠና ተጠናቋል፡፡


 

በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የተገኙት አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ስትራቴጂክ ግብ ተጥሎ እየተሠራ ይገኛል።


 

ሥልጠናው በፓርቲው መዋቅሮች በንብረት፣ በሰው ኃይልና በፋይናንስ አሥተዳደር ላይ ወጥነት ያለው ዘመናዊ አሠራር ለመዘርጋት የሚያግዝ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዋናው ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በሁሉም መዋቅሮች ላይ ባሉ ጽሕፈት ቤቶች ላይ ተግባራዊ በማድረግ የፓርቲውን አሠራር ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም ማርሻሎ፤ ሥልጠናው በፓርቲው ሀብትን በአግባቡ ለማሥተዳደር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች ዘመናዊ አሠራርን ለመዘርጋት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የግዥና ንብረት አሥተዳደር ዳይሬክተር ተመስገን ከተማ፤ ሥልጠናው አሠራሮችን ወጥ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

በክልሉ በፓርቲው ጽሕፈት ቤቶች የግዥና ንብረት አሥተዳደርን ለማዘመን ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቅው ሥልጠናው የጀመሩትን ሥራ ለማፋጠን እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፋይናንስና በጀት ቡድን መሪ አብዮት ታደለ በበኩላቸው፤ የወሰዱትን ሥልጠና በክልላቸው ባሉ የፓርቲው መዋቅሮች በማውረድም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም