ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተደረሰው የሰላም ስምምነት የተሳካ ውጤት እያመጣ ነው

ደብረ ብርሃን፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል መንግሥትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት የተሳካ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል።

የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች የማጠናቀቂያ መርሐ-ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደጀኔ ልመንህ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤በክልሉ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት የተሳካ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በመፍታት በየቀኑ እየገቡ መሆኑን ጠቁመው፥መንግሥትም የተሃድሶ ሥልጠና በመስጠት በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ መቀጠሉን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም ለልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ቀጣይነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

መንግሥት ለዘላቂ ሰላምና ልማት በትጋትና በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሥልጠና ዳይሬክተር ብርሃኑ ተስፋዬ ናቸው።

የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት የማቋቋም ሥራም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አስታውቀዋል።

የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው የተመረቁ የቀድሞ ታጣቂዎች በሚሰማሩበት የልማት መስክ ሁሉ ለሀገር ሰላምና ልማት የላቀ አበርክቶ እንደሚኖራቸውም አመላክተዋል።

ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ በመቆም መሥራት የዜጎች ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎችም የበደሉትን ሕዝብ በልማት ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውን ባወጡት ባለስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም