ባህላዊ ሥርዓቶች ውስጥ ያሉ የአብሮነት ዕሴቶችን ለሰላም ግንባታና ልማት መጠቀም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ ሥርዓቶች ውስጥ ያሉ የአብሮነት ዕሴቶችን ለሰላም ግንባታና ልማት መጠቀም ይገባል
ሸኮ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፦ ባህላዊ ሥርዓቶች ውስጥ ያሉ የአብሮነት እሴቶችን ለሰላም ግንባታና ልማት መጠቀም እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የሸኮ ዘመን መለወጫ እና የምስጋና በዓል "ቲካሻ ቤንጊ" በሸኮ ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች የራሳቸውን ባህል፣ ታሪክና ሥርዓት በማልማት የመጠቀም ልምድ እየተጠናከረ መጥቷል።
የሸኮ ዘመን መለወጫ "ቲካሻ ቤንጊ" የመተሳሰብ፣ የአብሮነትና የእርቅ ዕሴቶች እንዳለው ጠቅሰው እነዚህን እና ሌሎች ባህላዊ ሥርዓቶችን ጠብቆ ለሰላም ግንባታና ልማት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
አዝመራ ተሰብስቦ በጎተራ ከተከማቸ በኋላ የጥጋብና የደስታ ዘመን ማሳያ ተደርጎ የሚከበረው "ቲካሻ ቤንጊ" ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መጠናከር ትርጉም ያለው እንዲሆንም መስራት ይገባል ነው ያሉት።
ሸኮዎች ተፈጥሮን የሚንከባከቡበትና የባህላዊ ግጭት መፍቻ እውቀቶች ሳይበረዙ ለትውልድ በመሸጋገር ጥቅም እንዲሰጡ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ ባህላዊ ሥርዓቶች ያሏቸውን መልካም እሴቶች ለማጎልበት የክልሉ መንግሥት እኩል የመልማት ዕድል እንደሚያመቻችም ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቁመዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን "ቲካሻ ቤንጊ" አዲስ እህል በጋራ በመቅመስ የሚከበር የቀደምት አባቶች ሥርዓት ሲሆን ከምርትና ምርታማነት ጋር የተሳሰረ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተስማምቶ በሰላምና በፍቅር የመኖር ትርክት የሚነገርበት "ቲካሻ ቤንጊ" መከበሩ ጠቃሚ ዕሴቶች ለትውልድ እንዲተላለፉ አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራልም ብለዋል።
ሸኮዎች ከማኅበራዊ ሥርዓት ባሻገር ከተፈጥሮ ጋር ባላቸው ቁርኝት ጠብቀው ካቆዩት ደን ውስጥ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና እና ማር ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
የሸኮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሪ ጉሩሙ በበኩላቸው "ቲካሻ ቤንጊ" በዓል ስላለፈው አዝመራ እና የምርት ሁኔታ ምስጋና፥ ለቀጣይ ልማትም ልመና ለፈጣሪ የሚቀርበበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በበዓሉ ከጎረቤት ጋር ተሰባስቦ በመብላትና በመጠጣት ከማክበር ባሻገር ስለ አካባቢው መመካከርና ስለ ቀጣይ እርሻ ሥራ መመሪያና ምረቃ ከአባቶች የመቀበል ትውፊታዊ ሥርዓት እንዳለ ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለባህል ልማት በሰጠው ትኩረት እየተከበረ ባለው "የቲከሻ ቤንጊ" በዓልን በማልማት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ገዛኸኝ ኡፐም እና ታታሪ ዘካሪያስ ከሩቅም ከቅርብም በአንድ አደባባይ ተሰባስበን ማክበራችን አብሮነታችን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።
ተደብቀው የቆዩ ቱባ የባህል ሃብቶችን መጠቀም ከተቻለ የልማትና የተረጋጋ የሰላም ሁኔታን በጋራ መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል።