ቀጥታ፡

የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል-የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን

ኮምቦልቻ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፦የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮምሽነር ብርጋዲየር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው ገለፁ።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ሦስተኛውን ዙር የቀድሞ ታጣቂዎች የምርቃትና ሽኝት ፕሮግራም ዛሬ በኮምቦልቻ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል አካሂዷል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል መንግስትና በአፋህድ መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት መደረጉን ተከትሎ የታጣቂዎቹ አመራርና አባላት የሰላም አጋርነታቸውን በተግባር በማሳየት ትጥቃቸውን ፈትተው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅመው ዘላቂ ሰላምና ልማት መሆኑን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ የውስጥ አንድነትንና ሰላምን በማፅናት የኢትዮጵያን ሁለተናዊ እድገት በጋራ ማስቀጠል አለብን ብለዋል።


 

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት የማረጋገጥ ጥረት የተሳካ ውጤት መምጣቱን ገልፀዋል።

በክልሉ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በመፍታት በየቀኑ እየገቡ መሆኑን አንስተው፥በዘላቂነት የማቋቋም ስራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በክልሉ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ዛሬ ተመርቀው ወደ አካባቢያቸው እየተሸኙ መሆኑን ጠቁመው፣ ታጣቂዎች ህብረተሰቡን ሲቀላቀሉ ችግሮችን በመቋቋም ለክልሉ ልማት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።


 

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ፣ ለሀገርና ህዝብ ዘላቂ ሰላም ስንል የጥፋትን አማራጭ በመተው የሰላምን ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳችንን ተረድተናል ያሉት ማስረሻ ሰጤ ጥያቄዎቻንም የሚመለሱት በትጥቅ ትግል ሳይሆን በሰላም አማራጭ ብቻ መሆኑን ተረድተን መጥተናል ሲሉም ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የአፋህድ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ፣ ጥያቄዎቻችን ለማስመለስ ጫካ ብንገባም አዋጭ ባለመሆኑ የሰላምን አመራጭ ተቀብለን መጥተናል ብለዋል።

ከክልሉ መንግስት ጋር በፈጠርነው የሰላም ስምምነት ወደሰላም መጥተናል፤ አሁንም ጫካ ያሉ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡና ሰላም እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ዓመታት የክልላችንን ህዝብ በድለናል፣ኢኮኖሚውን አድቅቀናል ያሉት ኮሎኔሉ፣ ትግሉም በውጭ ሀይሎች ጭምር በመጠለፉ ሀገር አፍራሾችን አንተባበርም፣ መጠቀሚያም አንሆንም በማለት ሰላምን መርጠን መጥተናል ብለዋል።


 

በፕሮግራሙ የፌዴራል፣ የሀገር መከላከያ፣ የክልልና የዞን፣ እንዲሁም የፋኖ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም