ቀጥታ፡

አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ለኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶች ስኬትና ለፖሊሲ ግቦች መሳካት ቁልፍ ሚና የጫወታል-ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡-አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ለኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶች ስኬትና ለፖሊሲ ግቦች መሳካት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

‎አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ውጤት ይፋ ማድረጊያ አውደ ጥናት እየተካሔደ ነው።

ጥናቱ በእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ በቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም፣ በወሊድ መጠን፣ በጤና ተቋም የመውለድ ተሞክሮ፣ በሕፃናት ክትባት እና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳየች ላይ ያተኮረ ሲሆን የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተመላክቷል፡፡


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ ጥናቱ ከመደበኛ ስታቲስቲካዊ መረጃነት ባለፈ ለሀገራዊ ብልጽግና ጉዞ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያለው የፖሊሲ መሣሪያ ነው ብለዋል።

ጥናቱ መንግሥት ለልማት ዕቅዶች ስኬታማነት በመረጃ ላይ የተመሠረተ አሠራርን ለመከተል ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም አክለዋል።

ጥናቱ ከጤና ዘርፍ በዘለለ ሰፊ የማክሮ-ኢኮኖሚ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሯ የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለመገምገም እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሰው ኃይል ልማት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች የታዩ ለውጦችን በትክክል ለመለካት እንደሚያስችል ጠቅሰው፥ ጥናቱ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የተከተለ መሆኑ ለመረጃው ተዓማኒነትና ለዓለም አቀፍ አጋርነት ወሳኝ መሠረት እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥እውነተኛና ጥራት ያለው መረጃ የወደፊቱን የጤና ሥርዓት ውጤታማ ለማድረግ ዋነኛው መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በዘርፉ ሲተገበሩ የነበሩ መረጃዎች በአብዛኛው በግምትና በትንበያ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ አዲሱ ጥናት ግን ያለንበትን እውነታ በሐቀኝነት ለመገምገም እንደሚረዳና ለቀጣዩ የጤና ዘርፍ የኢንቨስትመንት ዕቅድ እንደ መነሻ እንደሚያገለግል አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት እንደ ኮቪድ-19 እና የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ቢገጥሟትም፣ ጥናቱ ሳይስተጓጎል እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጌጎ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ የጥናቱ ውጤት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂ የማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋትና የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ የሚረዳ ትልቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ውጤቱ የበርካታ ወገኖች የተቀናጀ ርብርብ ግኝት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ተዓማኒ መረጃን የማመንጨትና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ የመቅረጽ አቅሟን በተግባር ያረጋገጠችበት መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ዴስክ ኃላፊና የጥናቱ አቅራቢ አቶ ወርቅነህ ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ ጥናቱ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እና በቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀምና በወሊድ መጠን ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በጤና ተቋም የመውለድ ተሞክሮ፣ በሕፃናት መቀንጨር እና የሕፃናት ክትባትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችም የጥናቱ ትኩረት እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡‎

በጥናቱ ውጤት መሠረትም መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰው፥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም