ምሁራን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚናቸውን በይበልጥ ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚናቸውን በይበልጥ ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- ምሁራን የጋራ ትርክትን በማስረጽ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚናቸውን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ለልጆቻችን የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ምሁራን የወል ትርክትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለብን ሲሉም ገልጸዋል።
ምሁራን የነገዋን ኢትዮጵያ የሚቀርጹ ስትራቴጂካዊ መሐንዲሶች መሆናቸውን ገልጸው፤ ትውልድን በመቅረጽና የጋራ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ቀዳሚውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ቀደም ሲል የጋራ ማንነትን የሚገነቡ የወል ትርክቶች መዳከማቸው ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል።
ምሁራን በዝምታ ውስጥ በመሆን የታሪክ ተወቃሽ መሆን የለባቸውም፤ በመማር ማስተማር ሂደት ያሉ መምህራንም የተማሪዎችን ስብዕና እና ሀገራዊ ፍቅር በመገንባት ላይ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
የወል ትርክቶች ከታችኛው እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካተው ትውልዱ እንዲማርባቸው ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ምሁራን በትውልድ መካከል ድልድይ በመሆን የጋራ መግባቢያ ነጥቦችን ማፍለቅ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፤ ልዩነቶችን ወደ ውበት የሚቀይሩ ጥናታዊ ጽሑፎችንና ውይይቶችን ማበረታታት ይገባቸዋል ብለዋል።
የወል ትርክትን ማጎልበት የኅልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ምሁራን በያሉበት መስክ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።